ሕጋዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሌለው ምርጫ ለሙሰኞችና ለአፋኞቹ እንጂ ለሕዝብ አይበጅም--ትዴፓ

98

ሕጋዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሌለው ምርጫ ለሙሰኞችና ለአፋኞቹ መሪዎች ይበጅ እንደሆነ እንጂ ለህዝቡ የትም ስለማያደርስ ከወዲህ በግልጽ መቃወም እንደሚገባ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ተናገረ።

ፓርቲው ሕገ መንግሥትን የጣሰ ምርጫ ለምን? ሲል ያወጣውን መግለጫ ለኢዜአ ልኳል።

በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አፍላቂ፣ አርቃቂ፣ ፀሓፊና አጽዳቂ የህወሓት መሪዎች ለመሆናቸው ማንም ሰው አይስተውም የሚለው መግለጫው፤ የህወሓት መሪዎች እራሳቸው የፈጠሩት ሕገ-መንግስት መሆኑን የረሱት እስኪመስል ድረስ አጣመው ሲተረጉሙትና ሲሸሹት አልያም ሲጥሱት ማየቱ የተለመደ ሆኗል ብላል በመገለጫው።

ሕውሓቶች ገና ስልጣን ላይ እንደወጡ በ1983 ዓ/ም ጀምሮ የባሕር በር ጥያቄ ያቀረቡትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመግደል ነበር የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቱን የጀመሩት ብሏል ትዴፓ በመግለጫው ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አፈናው፣ ድብደባው፣ ግድያውና ያለፍርድ እስራቱ አሁን ድረስ ቀጥሎበታል የሚለው መግለጫው፤ ይህ እንደ መደበኛ አሠራር ያዳበሩት ክፉ ልምድ ብሎ  ብሎ አሁን አደገኛ ጫፍ ላይ በመድረሱ ሰላም፣ አንድነት፣ እኩልነትና ዕድገት የጠማው የኢትዮጵያ ህዝብ ተግቶ መፍትሄ ይሻ ዘንድ ይህን መግለጫ ማውጣት ግድ ሆኖብናል ብሏል ፓርቲው።

በቅድሚያ የወቅቱ አሳሳቢ ጉዳይ በሆነው ከሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ሕገ-መንግስቱ የደነገገውና የህወሓት መሪዎች የሚሉትን በንፅፅር እንመልከት ብሎ ይጀምራል መግለጫው ።

በአንቀጽ 102 መሰረት፣ ሕገ-መንግስቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ማቋቋሙንና ቦርዱም በፌደራልና በክልል ደረጃዎች ምርጫን የማስፈጸም ሃላፊነት እንደተሰጠው በግልጽ አስቀምጧል ይላል መግለጫው፡፡

ሕገ-መንግስቱ እንዲህ ቢልም በአንጻሩ የህወሓት መሪዎች ግን የክልሉ ምርጫ በገዛ እጃችን እናካሂዳለን በሚል ወዳ ወዲህ እያሉ ይገኛሉ ይልና ፓርቲው ።

ለምን? ብሎ ይጠይቀና መልሱ ቀላልና የማያሻማ እንደሆነ በማንሳት።

መልሱንም ባጭሩ ሕውሓቶች ያቀናበሩት ምርጫ ከተካሄደ እነሱ እራሳቸው አሸናፊዎች ተብለው ስልጣን ላይ እንደገና ብቅ እንደሚሉ ካለፉት ምርጫ ተብየ ቅንብሮችና “ተውኔቶች” ስለሚያውቁት ነው መሆኑን  በመግለጫው ጠቁሟል።

በዚህ ጊዜ በትግራይ ይቅርና፣ በመላ ኢትዮጵያ ምርጫ በምንም መልኩ ማካሄድ የሚችልበት ማኅበራዊ ብሎም ሕገ-መንግስታዊ ምክንያት እንደሌለው በመግለፅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማያሻማ መንገድ እንደገለጸላቸውም ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።

‘’በጥቂት አምባገነን መሪዎች የሚዘወረው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት’’ ግን ከዚህ ውሳኔ በፊትም ጀምሮ የትግራይ ፖለቲካዊ ምሕዳር ጥፍንግ አድርጎ በመያዝ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን የባሰ ዘግቶ የክልሉ ምርጫ ያለ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አካሂዳለሁ እያለ እንደሚገኝ ጠቁሟል።

ራሱን የመሰሉ ምስሌነ ድርጅቶች በመፈልፈል መጫወቻ ሜዳው ዴሞክራሲያዊ፣ ምርጫውም ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት ለማስመሰል ላይ ታች እያለ እንደሚገኝም ፓርቲው ይፋ አድርጓል፡፡

ራሱ የፈለፈላቸው ምስሌነ ድርጅቶች ከፋይናንሳዊ እገዛ ጀምሮ ጽሕፈት ቤቶች እንዲከፍቱ፣ በክልሉ ቴሌቪዥኖች እና ኤፍ ኤም ሬድዮዎች እንደፈለጉት እንዲለፍፉ እና ተፎካካሪ መስለው በመቅረብ ህዝብን እንዲያደናግሩ ሁኔታዎች አመቻችቶላቸዋል ይላል መግለጫው።

በሌላ ወገን ደግሞ ሌሎች ሕጋዊና ራሳቸውን የቻሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ትግራይ ውስጥ ገብተው የፖለቲካ ሥራዎች እንዳያሳልጡ የአምባገነኑ የህወሓት መዋቅር ብዙ እንቅፋቶች ተፈጥሮባቸዋል በማለት ቅሬታ ያቀርባል ብሏል ።

ሕውሓት ከፍረጃ ጀምሮ፣ ለጀሮ የሚከብዱ ስሞችን/ስድቦችን በመለጠፍ፣ ስብእናን በመግደል፣ አባላቶቻቸውን በመደብደብና በማሰር፣ ጽሕፈት ቤቶች እንዳይከፍቱ ከከፈቱም በማዘጋት የትግራይ ፖለቲካ ምህዳር በባሰ መልኩ ዘግቶታል ይላል መግለጫው።

የህዝብ ንብረት በሆኑት የትግራይ ሚድያዎች መቅረብ ለሕጋዊ ለሆነው ፓርቲዎች የማይታለም ነው የሚለው መግለጫው፤ዝርዝር ውስጥ ሳንገባ በሕውሓት በኩል በሕገ-መንግስቱ ክፍል አንድና ሁለት፣ ከአንቀጽ 14 እስከ 32 ያሉትን የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ድንጋጌዎች በመሉ ተጥሰዋል ማለቱ በቂ ነው በማለት ፓርቲው በመግለጫው ጠቁሟል።

‘አምባገነኑ ሕውሓት’ የፖለቲካ ምህዳሩን የባሰ በመወጠር ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ነጥቦች እየፈጸመ ይገኛል ይላል መግለጫው:-

  1. የ2012 ዓ/ም ክልላዊ ምርጫ ከማድረግ የሚያግደን ምንም ኃይል የለም በሚል ስርዓት-አልባ ውሳኔ አሳልፈው ከፍተኛ የሚድያ እና የአድርባይ ካድሬ ዘመቻዎች ጀምሯል። በሃገራችን ማናቸውም ክፍል ምርጫን የማካሄድና የመምራት ሕገ-መንግስታዊ ሉአላዊ ስልጣን የተሰጠውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን አልቀበልም ብለው ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ እየዛቱ ይገኛሉ።
  2. እነዛ የምርጫ ቦርድ ምስክር ወረቀት እንኳን የሌላቸውን እና የፈለፈሉዋቸውን ምስሌነ ፓርቲዎች በማሳተፍ እንዳለፉት 5 ምርጫዎች የውሸት ምርጫ በማካሄድ አሁንም የትግራይ አይነኬ ገዢዎች ለመሆን በመቋመጥ ወገባቸውን አስረው እየሰሩ ነው።  
  3. አሃዳዊና ጨፍላቂ መንግሥት መጣብህ በማለት በባሰ መልኩ ህዝቡን በማደናገርና በማስፈራራት ህዝቡን ከፌደራል መንግስቱ ጋር ጦርነት ውስጥ ለማስገባትና በሰበቡ ሥልጣንቸውን ለማራዘም በሚል ስሌት ቀቢፀ-ተስፋ እርምጃዎች በመሰንዘር ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ።
  4. በሌለ ጠላት «ተከበሃል» የሚል ልበ-ወለዳዊ ትርክት በመፍጠር ከጎረቤት ወንድም ህዝቦች ጋር ወደ ጦርነት ሊያስገቡት የጦርነት ነጋሪት እያወጁ ይገኛሉ።
  5. በዚህ ሳምንት ደግሞ በትግራይ ያሉ የእውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ስም ዝርዝርን በማውጣት ህዝቡ በነዚሁ አባላት ላይ በሆነ መልኩ የማስወገድ እርምጃ እንዲወስድባቸው በማነሳሳት ላይ ይገኛሉ።
  6. በሌላ በኩልም በመሐል አገር ያሉ አንዳንድ ፓርቲዎች በማፈላለግ ከአምባገነኑ የህወሓት አመራር ጋር እንዲወግኑ በማግባባት፣ በሁለቱ ምክርቤቶች የፀደቀውን የሕገ-መንግሥት ትርጉም ውሳኔን በህገ-ወጥነት እንዲቃወሙና አገሪቱን በማበጣበጥ በአቋራጭ ሥልጣንን ለመቆጣጠር ያለመ ህዝቡን የማደናገር እና ህዝቡ በፌደራል መንግሥቱ ላይ አሉታዊ ግንዛቤ እንዲኖረው እያደረጉ ይገኛሉ በማለት ቅሬታውን ያቀርባል መግለጫው።

በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ መስተጋብር ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ነው የሚለው መግለጫው፤ በአምባገነኑ እና «የበሰበሰው» የህወሓት አመራር የሚዘወረው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግሥት እስካሁን የሄደበት የፖለቲካ ጉዞ እጅግ ትእግስት የበዛበትና የሚመሰገን ነው ብሏል። ሆኖም ግን ሙሰኛው እና ጨፍላቂው የህወሓት አመራር በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት እየተጓዘበት ያለው መንገድ የትግራይ

ሕዝብንና ክልሉን ብቻ ሳይሆን የተቀረውን የኢትዮጵያ ሉአላዊነትንና ህዝቡን የሚጎዳ ብሎም የአገሪቱ ሁለንተናዊ ሰላም በመሸርሸር ላይ መሆኑ «ፌዴራላዊ ጥምረት» እያለ ከሚያሰማራቸው ፀረ-ለውጥ ቡድኖች እንቅስቃሴ መገንዘብ አይከብድም ይላል መግለጫው።

ይህ ሃገርን የሚያናጋ አደገኛ ሂደት በወቅቱ ካልተገታ ለእርስበርስ እልቂት የሚዳርግ ለመሆኑ እሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤቶቻችን አናጣውም የሚለው መግለጫው፤ መንግሥት ጉዳዩን ሃይ ማለት እነዳለበት ጥሪ አቅርቧል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 51 ቁ. 1 እና ቁ. 6 መሰረት ግዴታ ስላለበት፣ ለሃገር ደህንነት ሲባል ጊዜ ሳያባክን በዚህ መርዘኛ ቡድን ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት አበክሮ እንደሚያሳስብ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል።

ፓርቲው ለትግራይ ሕዝብም ጥሪ አቅርቧል።

በስምህና በልጆችህ መስዋእትነት እየማሉና እያላገጡ፣ በመላ ኢትዮጵያ አፈና፣ ሙስና፣ ድህነትና የርስበርስ ግጭት እንዲስፋፋ ያደረጉት ስግብግቦቹ የህወሓት መሪዎች የለውጥ አየር ስለመጣባቸው ወደ መቐለ በመሸሽ፣ «ጠላት መጣብህ! ተከበሃል! ታጠቅ! ተከላከል!» እያሉ እረፍት እንደነሱህ ራስህ ታውቀዋለህ ይላል መግለጫው።

የከበበህም ይሁን የሚመጣብህ ጠላት የለም። ውሸት ነው። ይህ ሁሉ ውሸት ግን ዓላማ አለው። በመላ ኢትዮጵያ የነፈሰው የለውጥ አየር ትግራይ ውስጥ ተጋብቶ ህዝብ በነጻ ውይይት እንዳይለበልባቸው ለመከላከልና በለመዱት ስልጣን ላይ ለመሰንበት ታስቦ ነው በማለት መግለጫው ያሳስባል።

እነሱና ልጆቻቸው ስልጣንን መከታ አድርገው ባካበቱት ሃብት በምቾት ሊኖሩ፣ አንተና ልጆችህ ግን እየሞትክና እየቆሰልክ ተከላካይ ልትሆንላቸው አስልተው ነው የሚለው መግለጫው፤ ለዚህ ነው «ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው» እያሉ ጧትና ማታ የሚዘፍኑልህ ይላል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም፣ ተገንጥለን የራሳችን መንግስት (de facto state) መስርተን እንምራህ ይላሉ የሚለው መግለጫው፤ የ29 ዓመታት አስከፊ አገዛዛቸው መላው ኢትዮጵያዊ እንዳላንገሸገሸው ሁሉ፣ ኣሁንም ለብቻቸው ተነጥለው የክልል ምርጫ ለማካሄድና በለመዱት አፋኝ አገዛዝ ሊቀጥሉ ይንደፋደፋሉ ይላል ፓርቲው።

ማን ከማን ነው የሚገነጠለው? የሚለው ፓርቲው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በትውልድ፣ በታሪክ፣ በባህል፣ በስነ-ልቦና እንዲሁም በፖለቲካ-ኢኮኖሚ የተቆራኘና ለመገንጠል የማይቻል ሀዝብ ነው ሲል ይጠቅሳል።

ከየት ወዴትስ ነው የሚገነጠለው? በስልጣን ያኮረፈ ሁሉ ልገንጠል ቢል ገደቡስ የት ላይ ነው? የመገንጠል ፋይዳውስ ምንድን ነው? ሰላም፣ ፍትሕና ዕድገት ከተፈለገም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት እንጂ በመገንጠል እንደማይገኙ እሩቅ ሳንሄድ ጎረቤቶቻችንን ማየት በቂ ነው ይላል መግለጫው።

ስለዚህ የተናጠል ምርጫ ማካሄድ ሕገ-መንግሥቱን የሚጥስ ከመሆኑ ባሻገር፣ ተነጥሎ ለመኖር ሽሽት ላይ ላሉት፣ ወኔ የራቃቸው ሙሰኞቹ የህወሓት መሪዎች ጊዚያዊ መደበቂያ ይሆናቸው እንደሆን እንጂ ለትግራይ ህዝብ ምንም ዓይነት እርባና እንደሌለው ሊታወቅ ይገባል ሲል መግለጫው ያሳስባል።

ትልቅ ሃገር እየገዙ ያላመጡት ሰላም፣ ፍትሕና ዕድገት፤ ትንሽ ሃገር መስርተው ያመጡታል ማለት ዘበት ነው የሚለው መግለጫው፤ “ሌብነት ሥራ ነው፣ ከተያዝክ ግና ወንጀል ነው” ብለው የሚስብኩ፣ “ለህክምና የተሰራ ህንፃ እዚህ ነበረ፣አሁን ግን ጠፋ” ብለው ሪፖርት የሚያቀርቡናቸው ይላል መግለጫው።

እንደነ አለማት አማረ (የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ም/ሓላፊ) ለህዝብ መብት መከበር የቆሙትን ሁሉ “ባንዳዎች” ብላ የምትዘነጥል፣ ዋልጌ እና ምግባረ ብልሹ መሪዎች ፤  ሁሌም በመከራ፣ ስደት፣ ግጭትና አፈና ሊያኖሩህ ካልሆነ በስተቀር ለችግርህ መፍትሄ ስለማይሆኑ፣ እነሱን በሰላማዊ መንገድ በማስወገድ የራስህን ዕድል በራስህ ወሳኝ የምትሆንበትን ስርዓት ለመፍጠር ተደራጅተህ ታገል እንላለን ሲል መግለጫው ጥሪ ያቀርባል።

ሕጋዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የሌለው ምርጫ ለሙሰኞችና ለአፋኞቹ መሪዎች ይበጅ እንደሆነ እንጂ ለህዝቡ የትም ስለማያደርስ ከወዲህ በግልጽ መቃወምና ያሰቡት የመንደር ምርጫው ማስቆም ያስፈልጋል ብሏል ፓርቲው በመግለጫው።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምን ጊዜም ከጎንህ ላይ ቆሞ፣ ሁሉንም በእኩልነት አሳታፊ ሕገ-መንግስታዊ ምርጫ ተካሂዶ፤ ሰላም፣ ፍትሕና ዕድገት፤ የሚሰፍንበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ እንዲመሰረት ትግሉ በአጽንኦት እንደሚቀጥል መግለጫው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም