በደቡብ ወሎ ዞን 31 ሚሊዮን ብር በድጋፍ ተገኘ

1045

ደሴ ፣ ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ 31 ሚሊዮን ብር እና ከአምስት ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል በድጋፍ መገኘቱን የዞኑ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ግብረ ኃይሉ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የሚገኙ የኮሮና ቫይረስ የህክምና ማዕከልና የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ዛሬ ጎብኝቷል፤ለጤና ባለሙያዎች ማበረታቻዎችን አበርክቷል፡፡

የዞኑ  ዋና አስተዳዳሪና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ሰይድ መሃመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ቫይረሱ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረትም  31 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና ከአምስት ሺህ ኩንታል በላይ የተለያየ ዓይነት የምግብ እህል መገኘቱን ተናግረዋል።

በዞኑ በተደረገው አሰሳ  ከ102 ሺህ በላይ አቅመ ደካሞች የተለዩ  መሆኑን አመልክተው እስካሁን 15 ሺህ ለሚሆኑ ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

ከሃብት ማሰባሰቡ በተጓዳኝ በጤና ባለሙያዎች የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ግንዛቤ የሚፈጥሩና የሚያስተባብሩ ተግባር  በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማሰማራት እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በየወረዳው  ህብረተሰቡን  በማስተባበር  ለአቅመ ደካሞች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የምግብ እህል ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በቦሩ ሜዳ ሆስፒታልና ኮምቦልቻ ለይቶ ማቆያ ጉበኝት ባደረገበት ወቅት ከ50ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው በግ ፣ ማርና   ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለጤና ባለሙያዎች በማበረታቻነት አበርክቷል።

የቦሩ ሜዳ ሆስፒታል ስራ ስራአስኪያጅ  አቶ ሲሳይ ተበጀ በበኩላቸው፤ ለተደረገላቸው ማበረታቻ   አመስግነው ይህም ጤና ባለሙያዎች  ተግተው እንዲሠሩ ይበልጥ የሚያነሳሳ  መሆኑን ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ኮሮና  መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሰባቢ ዶክተር ከማል አህመድ ወረርሽኙ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማቃለል ሁላችንም ተባብረንና ተጋግዘን ይህን ክፉ ቀን ማለፍ ይጠበቅብናል ብለዋል፡

በጉብኝቱ  የደቡብ ወሎ ዞን አመራሮች፤ ጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።