የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ችግኝ ተከሉ

199

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ችግኝ ተከሉ።

የተቋማቱ አረንጓዴ አሻራ አካል የሆነው መርሀ ግብር በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ችግኞችን በመትከል ተከናውኗል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት “የተተከሉት ችግኞች ለፍሬ ሊደርሱ የሚችሉት በሚደረግላቸው እንክብካቤ ነው።”

ባለፈው አመት በሁለት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ 20 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰው ከነዚህም 80 በመቶ የሚሆኑት ጸድቀዋል ብለዋል።

ዘንድሮም አጠቃላይ የተጠሪ ተቋማትን ሰራተኞች በማስተባበር 20 ሺህ ችግኞችን እንተክላለን ብለዋል።

ለዚህም በዛሬው እለት ብቻ 2 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ እስከ 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች የአካባቢ ብክለት እንዳያመጡ የአረንጓዴ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንም ነው ሚኒስትሩ የጠቆሙት።

ከችግኝ ተከላው በኋላም ሰራተኞቹ ደማቸውን ለግሰዋል።