በኢትዮጵያ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል የመንግስትና ሲቪክ ማህበራት ትብብር አስፈላጊ ነው

112

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋሉ ማህበረሰባዊ ችግሮችን ለማቃለል የመንግስትና ሲቪክ ማህበራት ትብብር መጎልበት እንዳለበት የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ “ፕሮጃይኒስት” ከተባለ ሀገር በቀል ሲቪክ ማህበር ጋር በማህበራዊና ሰላም ጉዳዮች ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ ወቅት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን፤ ማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለልና ሰላምን ለማስፈን የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን መከላከል ልዩ ትኩረት የተደረገ ቢሆንም በቀጣይም የተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮችን ለማቃለል መንግስትና የሲቪክ ማህበራት ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በማህበረሰባዊ ጉዳዮች፣ የሰላምና ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠል የኖርበታልም ነው ያሉት።

ሰላም ሚኒስቴርና ፕሮጃይኒስት በደረሱት ስምምነት መሰረት ኮቪድ- 19ን ለመከላከል ከወጣቶች ጋር ትብብርና ድጋፍ በማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ይኖራሉ።

የፕሮጃይኒስት ዳይሬክተር ወይዘሮ ነፃነት መንግስቱ እንዳሉትም ተቋማቸው በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅርበትና በትብብር ይሰራል።

የፕሮጃይኒስት ሀገር በቀል የሲቪክ ማህበር የ7 ሲቪክ ማህበራት ስብስብ ሲሆን የማሳያ ስራውን በቅርቡ በአዲስ አበባ ይጀምራል።