አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ ሴናተሮች ጥሪ አቀረቡ

61

ሰኔ 22/2012(ኢዜአ) አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ ሁለት የአሜሪካ ሴናተሮች ለሀገሪቱ ግምጃ ቤት በላኩት ደብዳቤ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሴናተር ኮሪ ቡከር እና ሴናተር ክርስቶፎር ኩንስ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን መኑሸን በላኩት ደብዳቤ ሀገራቸው በግድቡ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር በያዘችው አቋም ገለልተኛ አንድትሆን ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ አቅም እየገነባች ያለው የኃይል ማመንጫ ግድብ ራሷን ከድህነት ለማላቀቅ የምታደርገው ጥረት አካል መሆኑን የገለጹት ሴናተሮቹ፤ ግንባታው ግን በሀገራቱ ለድፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከር ምክንያትና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠናው ሰላም ስጋት ሆኗል ብለዋል፡፡

አሜሪካ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ተዋናይና ምክንያት ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባት አሳሰበው፤ ሶስቱም ሀገራት ችግሮቻቸውንና አለምግባባቶችን በድፕሎማሲያው መንገድ እንዲፈቱ ማበረታታ እንደሚገባትም ነው የጠየቁት፡፡

ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ያሏቸውን አለመግባባቶች ለመፍታት ወደ የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዱ ትክክለኛ ቦታው አይደለም ያሉት ሴናተሮቹ ወደፊትም በሁሉም ሀገራት ዘንድ ተቀባይት ያለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ መፍትሄ ለማግኘት መስራት እንደሚገባት መጠየቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም