በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ የዋግ በሽታ በጤፍና ስንዴ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

93

ነገሌ፣ ሰኔ 22/2012 (ኢዜአ) በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ የተከሰተው የዋግ በሽታ በበልግ አዝመራ በተዘራው የጤፍና የስንዴ ሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አንዳንድ የወረዳው አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት በበኩሉ ተከሰተ የተባለው በሽታ አይነትና የሚያደርሰው የጉዳት መጠን በባለሙያ እየተጠና ነው ብሏል፡፡

በወረዳው የዲቤ ጉቼ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዲዳ ቦሩ በሰጡት አስተያየት በስንዴ ሰብላቸው ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት የተከሰተው የዋግ በሽታ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

ከነገሌ ከተማ ከአንድ ግለሰብ ሱቅ አንዱን ሊትር መድሀኒት በአንድ ሺህ ብር ገዝተው ለመከላከል ጥረት ቢያደርጉም በሽታውን ማጥፋት አልተቻለም ብለዋል፡፡

በሽታውን በጊዜ መከላከል ካልተቻለ በበልግ አዝመራ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የጤፍና የስንዴ ሰብል ምርት ሊቀንስብኝ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለባቸው ገልፀዋል ።

የነገሌ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር መለሰ ሽፈራው በበኩላቸው የዋግ በሽታው ያደረሰውን ጉዳት ለግብርና ባለሙያዎች ቢያሳውቁም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግስት በአፋጣኝ መድሀኒት ካላቀረበ በሽታው በተለይ በስንዴ ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለባቸው ።

የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ወጣት አበራ ሞገስ እንዳለው ደግሞ አሁን በገበያ ላይ ያለውን የዋግ መድሀኒት ገዝቶ ቢጠቀምም በሽታውን የመከላከል አቅሙ ደካማ ነው ብሏል፡፡

በጉጂ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሊበን ቦሩ በጉዳዩ ዙርያ በሰጡት አስተያየት በዞኑ ሊበን ወረዳ በበልግ አዝመራ 35 ሺህ ሄክታር መሬት በጤፍና በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በወረዳው ከአንድ ሳምንት በፊት በሰብል ላይ ተከሰተ የተባለውን የዋግ በሽታ ለመከላከልና ትክክለኛውን መድሀኒት ለማቅረብ በበላሙያ ጥናትና ቅኝት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን በተደረገ የባለሙያ ምልከታ ውሀ በተኛበትና ዘር በበዛበት ሰብል ላይ ብቻ የተከሰተ በመሆኑ እምብዛም እንደማያሰጋ ገልጸዋል፡፡

ተከሰተ የተባለው በሽታ ምንነትና የሚያደርሰው የጉዳት መጠን ከተረጋገጠ ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድሀኒት ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጁነት  መኖሩን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም