የፍቼ ከተማና አካባቢው ተወላጆች ለችግር ለተጋለጡ ወገኖቻቸው 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

77

ፍቼ፣  ሰኔ 21/2012 (ኢዜአ) የፍቼ ከተማና አካባቢው ተወላጆች በከተማው በኮቪድ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎችና ለከተማ አስተዳደሩ የ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉ በከተማው በኮቪድ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ነዋሪዎችና በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ሶስት ቢሮዎች የተሰጠ ነው ።

ድጋፉ የተሰባሰበው በሰላሌ ተወላጆች ህብረት ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ ሲሆን  የኮሚቴው ሰብሳቢና የግራር ጃርሶ ወረዳ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ አባል ወይዘሮ ፀሐይ ደምሴ እንዳሉት ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ጊዜያዊ የምግብ ቀለብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ያካተተ ነው ።

ኮሚቴው ከአካባቢው ተወላጆች በተጨማሪ ከአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ከሚገኙ በጎ አድራጊዎች ያሰባሰበው ድጋፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

በድጋፉ ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ከተገኙት የአካባቢው ተወላጆች መካከል አርቲስት አብረሃም ወልዴ በሰጠው አስተያየት በፍቅርና በወዳጅነት መንፈስ ያሳደገን የህብረተሰብ ክፍል ሲጎዳና ሲቸገር ማየት ስለማልፈልግ ለወደፊቱም ድጋፌን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረኃይል አባል አቶ ክፍሉ ከበደ በበኩላቸው ተወላጆቹ ያደረጉት ድጋፍ የተቸገሩ  ህብረተሰብ ክፍሎችን የሚታደግ በመሆኑ ለወደፊቱም  ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል ።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከል የቀበሌ 01 ነዋሪና የቀን ሰራተኛዋ ወይዘሮ ፅጌ ነገዎም  የአካባቢው ተወላጆች በችግርና በበሽታው ወቅት ላደረጉላቸው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል ።

በዚሁ ቀበሌ በእንጀራ ንግድ ሲተዳደሩ የነበሩት የአራት ልጆች እናት ወይዘሮ የኋላሸት ጅማ በበኩላቸው የተደረገላቸው ድጋፍ ጊዜያዊ ችግራቸውን የሚያቃልልላቸው ከመሆኑም ባሻገር የአካባቢው ተወላጆች ለነዋሪዎቹ ያላቸውን ክብርና ፍቅር የገለጹበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል ።

በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙ እንግዶች የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሄደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም