ፓርቲዎች የህዳሴ ግድቡን በመሳሰሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ ተጠየቀ

67

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ( ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመሳሰሉ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ ተጠየቀ።

ምርጫ ይካሄድ የሚሉ አካላትም ለህዝብ ህልውና ቅድሚያ በመስጠት  የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የትግራይ ተወላጆች እንዳሉት፤ በአሁን ሰአት ከምንም ነገር ይልቅ ቅድሚያ ወረርሽኙን ለመከላከል መሰጠት አለበት። 

''የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ወሳኝና የህልውና ጉዳይ ነው'' ያሉት የክልሉ ተወላጅ የሆኑት ወይዘሮ መድህን ገብረመስቀል፤ ሁሉም ፓርቲዎችና አገሪቱን የሚደግፉ አካላት በሙሉ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ በትብብር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

አቶ ታሪኩ  አድሃና በበኩላቸው የህዳሴው ግብድ የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያዊያን ፕሮጀክት በመሆኑ ሁሉም ኃይል ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው ለፍፃሜው መረባረብ እንዳለበት ገልፀዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት ምርጫን ማካሄድ ተገቢነትና ተቀባይነት እንደሌለው ገልጸዋል።

''ምርጫ ይካሄድ የሚሉ የትግራይ ክልል አመራሮች ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል'' ብለዋል።

የወረርሽኙን ሁኔታ ወደ ጎን በመተው ምርጫው ቢካሄድ እንኳን የፖለቲካ ምህዳሩ ባልሰፋበት ሁኔታ አንድ ፓርቲ ብቻውን መወዳደር ስለማይችል የህወሃት አመራሮች የያዙት አቋም የማያስኬድ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም