የአምባርቾ ተራራን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

48

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ( ኢዜአ) በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዱራሜ ከተማ የሚገኘውን የአምባርቾ ተራራን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና የቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት የዞኑን የቱሪስት መስህቦች ማልማት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ መነዶ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአምባርቾ ተራራን ጨምሮ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ሃብቶች አሉ።

እነዚህን ሃብቶች የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በዞኑ በርካታ የቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ሃብቶች የመኖራቸውን ያህል በቂ ስራ ባለመሰራቱ ከዘርፉ ጥቅም ሳይገኝ መቆየቱን ተናግረዋል።

''ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የአምባርቾ ተራራን ጨምሮ ሌሎች የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን በማልማት ለቱሪዝም ገበያ ለማቅረብና ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

ይህም አካባቢውን ተጠቃሚ ከማድረግ አልፎ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

የአምባርቾ ተራራ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን የተፈጥሮ ሃብት እና የመሰረተ ልማት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ''በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ብዙ ያልታወቁና መጎብኘት ያለባቸው ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራዎች አሉ'' ብለዋል።

እነዚህን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ የመስራትና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በከምባታ ጠምባሮ ዞን የቱሪዝም ስፍራዎችን ለማልማት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የቱሪዝም ኢትዮጵያ እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

ከውይይቱ በኋላ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሚኖረው መርሃ ግብር የአምባርቾ ተራራን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎች እንደሚጎበኙም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም