ሠራተኞቹ በአውቶቡስ ተርሚናሉ ግንባታ መጓተት ለችግር ተዳርገዋል

172

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 (ኢዜአ) የመርካቶ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ የድርጅቱ ሠራተኞች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የአውቶቡስ ተርሚናሉን በመጪዎቹ ሶስት ወራት ለማጠናቀቅ እየሰራሁ ነው ብሏል።

በአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት የአዲስ ከተማ መቆጣጠሪያ የስምሪት አስተባባሪ አቶ መርሳ ለገሰ በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአውቶቡስ ተጠቃሚ መኖሩን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ሠራተኞቹ ቀድሞ ይሰሩበት የነበረው የአውቶቡስ ማቆሚያ በቶሎ ባለመጠናቀቁ ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውን ነው የጠቆሙት።

አንበሳ አውቶቡስ ከዚህ በፊት ከሚያሳፍረው ሕዝብ ቀንሶ ከአቅም በታች እየሠራ፤ የተጠቃሚው ቁጥር ግን እያደገ መምጣቱ ለከፍተኛ መጨናነቅ መዳረጉንም ገልጸዋል።

ከመቶ በላይ አውቶቡሶች በ29 መስመሮች ወደ አካባቢው እንደሚመጡና መቆሚያ በማጣት ለከፍተኛ መጨናነቅ እንደሚዳረጉም ነው የጠቆሙት።

ይህም ሠራተኞቹን በተለይ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽን ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ በቶሎ ተጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚመለከተው ክፍል ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ዘመናዊ ማሳፈሪያ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ኅብረተሰቡም ሆነ የአንበሳ አውቶቡስ ሠራተኞች ችግር ላይ ወድቀዋል ነው ያሉት።

የድርጅቱ የድንገተኛ ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ሙልዬ ወልዴ በበኩላቸው፣ በአካባቢው አውቶቡስ ለመሳፈር በሚፈጠረው ግፊያና መተሻሸት ኅብረተሰቡ ለኮሮና ወረርኝኝ ተጠቂ እንዳይሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ ጫና በማሳደሩ መንግስት ኅብረተሰቡ ለኮረናቫይረስ እንዳይጋለጥ ፕሮጀክቱን በፍጥነት ወደ ስራ ያስገባ ሲሉም ጠይቀዋል።

በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ናትናኤል ጫላ መንግሥት በመደበው ከፍተኛ በጀት ግንባታው በመከናወን ላይ የሚገኘው ባለሁለት ወለል የከተማ አውቶቡስ ተርሚናል ሥራ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ለግንባታው መዘግየትም የተጨማሪ ስራዎች መምጣት፣ የበጀት በወቅቱ አለመለቀቅና ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በጊዜው አለመድረስ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል።

የአካባቢው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ አዳጋች እንዳደረገውም አክለዋል።

ከተማ አስተዳደሩና ማዘጋጃ ቤቱ በሰጡት ልዩ ትኩረት ፕሮጀክቱን በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ተርሚናሉ ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ ሃያ አውቶቡሶችን በማስተናገድ በሠዓት ለስድስት ሺህ መንገደኞች ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።