የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ 3ቱ አገሮች ለድርድሩ ያሳዩትን ፍላጎትና ድጋፍ አድንቋል

192

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ቢሮ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በቪዲዮ ኮንፈረንስ የታገዘ ውይይት ካደረገ በኋላ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ለተደረገው ድርድር ያሳዩትን ፍላጎትና ድጋፍ አድንቋል።

ሶስቱም አገሮች በድርድሩ ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት ያሳዩትን ገንቢና  አዎንታዊ ቁርጠኝነትም አድንቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሶስቱም አካላት በድርድሩ ሂደት ሁሉንም የሚያግባባ የቴክኒክና የህግ ጉዳዮችን የተመለከተ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያስቀምጡ ጠይቋል።

አገሮቹ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ድርድር ውስብስብ ከሚያደርጉ አስተያየቶችና እርምጃዎች ለመቆጠብ ያሳዩትን ተነሳሽነት ህብረቱ አድንቋል፡፡

ሶስቱ አገሮች በህብረቱ  አማካኝነት በሚደረገው ድርድር ለመሳተፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ለቢሮው ባቀረቡት ሪፖርት በህዳሴ ግድብ ላይ የሶስቱ አገሮች ድርድር 90 በመቶ እንደተፈታ ማሳወቃቸውን አድንቋል፡፡

በግድቡ ቴክኒካዊና ሕጋዊ ጉዳዮች ላይ ሶስቱን አገሮች ያቀፈና የህብረቱ ኤክስፐርቶች የሚሳተፉበትና ደቡብ አፍሪካ የህብረቱ ሊቀመንበር በመሆኗ በታዛቢነት የምትሳተፍበት ኮሚቴ እንደሚቋቋምና ኮሚቴው ይህን መግለጫ ካወጣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሪፖርቱን ለህብረቱ ሊቀመንበር ያቀርባል ተብሏል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አገሮች መሪዎችና መንግስታት  በህዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገው ድርድር በህብረቱ መሪነት እየተካሄደ መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት እንዲያውቀው አድርገዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአፍሪካ ህብረት ዘላቂ መፍትሔ እንዲያስቀምጥ በአደራዳሪነት መሰለፋቸውን ተከትሎ አድናቆቱን ገልጾላቸዋል፡፡

በድርድሩ የተሳተፉ አገሮች መሪዎችና መንግስታት ይህ መግለጫ ከወጣ ከሁለት ሳምንት በኋላ በድርድሩ የተገኘውን ውጤት የሚገልጸውን ሪፖርት  ለመገምገም ቀጠሮ መያዛቸው ተገልጿል፡፡

ውይይቱ በአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት ተከናውኗል።

በውይይቱ  የህብረቱ ልዩ የመሪዎች ጠቅላላ ጉባኤ ቢሮ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ሲሸካዲ፣ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የማሊ ፕሬዚዳንት ኢብራህም ቡበከር  ኬይታ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ  እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ተሳትፈዋል፡፡

ቢሮው የሶስቱ አገሮች መሪዎች በትብብር መንፈስ ሰላማዊና ለድርድር የሚመቹና ሁሉንም አካላት አሸናፊ የሚያደርጉ ሀሳቦችን በማቅረባቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡