መሪዎቹ ስምምነት ላይ የደረሱት የቴክኒክ ቡድኑ በሁለት ሳምንት ሪፖርቱን ጨርሶ እንዲያቀርብ ነው-ሚኒስትር ስለሺ

52

ሰኔ 20/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን መሪዎች በቪዲዮ ባደረጉት ውይይት የቴክኒክ ቡድኑ በሁለት ሳምንታት ሪፖርቱን ጨርሶ እንዲያቀርብ መስማማታቸውን የውሃ፤ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኅብረተሰቡ የግድቡ ውሃ ሙሌት በሚገልጹ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዳይደናገሩም ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

በአፍሪካ ኅብረት አዘጋጅነት መሪዎቹ ትናንት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌትና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ በኢትዮጵያ ታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ምክክር አካሂደዋል።

ምክክሩ የተዘጋጀው በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሲሆን፣ የጉባኤው አባላት የኬንያ፣ የማሊና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ 

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለግድቡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ትናንት ስለተካሄደው የመሪዎች ውይይት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እንዲሁም ተጨማሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች ተካተው የቴክኒክ ቡድኑ በሁለት ሳምንታት ሪፖርቱን እንዲያቀርብ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

እስከዚያው ግድቡ ውሃ ለመሙላት የሚያስችለውን ግንባታ የማጠናቀቂያ ሥራዎች ለአፍታም ሳይቋረጡ ይቀጥላሉ ብለዋል።

ውይይቱ ከውሃ መሙላት ጋር ተያይዞ ምንም ብዥታ እንዳልተጠረበትና ግድቡ ውሃ መሙላት እስኪችል ግንባታው ለሰከንድ እንደማይቋረጥ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ችግር በአፍሪካ መፍትሄ እንዲያገኝ በማሰብ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት መመለሱ ለኢትዮጵያ ድል መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

ኢትዮጵያ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዲዘገይ የተስማማች አድርገው በሚወጢ የሐሰት መረጃዎች ኅብረተሰቡ እንደማይደናገሩ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የግብጽ መገናኛ ብዙኃን የግድቡን ጉዳይ በለመዱት መንገድ አጣመው መጻፍ ልማዳቸው መሆኑን በማስታወስ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም