ከተለያዩ ተቋማት ለቋሚ ኮሚቴዎች የሚቀርቡ የሐሰት ሪፖርቶች እየቀነሱ መጥተዋል-የአዲስ አበባ ምክር ቤት

66
አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010 የአዲስ አበባ ምክር ቤት በተቋማት ላይ የሚያካሄደውን የቁጥጥርና ክትትል ስራውን እያጠናከረ በመምጣቱ የሚቀርቡለት የሐሰት ሪፖርቶች እንዲቀንሱ እያደረገ መምጣቱን አስታወቀ። ምክር ቤቱ ዛሬ በጀመረው 5ኛ የሰራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ዓመታዊ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት እንደገለጸው የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች፣ ቢሮዎች፣ ኤጀንሲዎች፣የባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ምክር ቤቱ የሚሰጣቸውን ግብረ መልሶችን እየተቀበሉ የተስተካከለ ሪፖርት ማቅረብ ጀምረዋል። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ አቶ ተስፋዬ ተርፋሳ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ምክር ቤቱ የሚያካሄደውን የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች መጨመሩ ታቅዶ ያልተፈጸሙ ተግባራትን በተጨባጭ ለመለየት አስችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ይመጡ የነበሩ የሐሰት ሪፖርቶች እንዲቀንሱ አስተዋጽጾ አድርጓል ብለዋል። ቋሚ ኮሚቴዎች የተጠናከረ የመስክ ምልከታና ሱፐርቪዥን ማካሔዳቸው በተግባር ሳይሰሩ የሚቀርቡ ሪፖርቶች እንዲታረሙ ማድረጉን ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ባለፉት አምስት ዓመታት 16 መደበኛና አንድ አስቸኳይ ጉባዔ ማካሄዱንና 59 አዋጆችን በማውጣት ስራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉንም ገልጸዋል። በምክር ቤቱ አባላትን በአመራር ቦታ ላይ የመመደብና ቋሚ ኮሚቴዎችን በማዋቀር በኩል ያሉ ችግሮች ግን ሙሉ በሙሉ እንዳልተፈቱም በውይይቱ ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል። የአስፈጻሚው የቁጥጥርና ክትትል ስራን በትርፍ ጊዜ ብቻ መስራትና የምክር ቤቱ አባላት በጉባዔው ላይ አለመገኘት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በድክመት መታየቱንም ገልፀዋል። ብዙሃን ድርጅቶችና የሙያ ማህበራትን በማሳተፍ በሚቀርቡ ግበረ መልሶች መሰረት እርምጃ መውሰድና በዲሞክራሲ ከዳበሩ አገራት ተሞክሮ በመውሰድ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በሚል ቀርበዋል። ምክር ቤቱ ዛሬ የጀመረውና እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም በሚያደርገው ጉባዔው የከተማ አስተዳደሩን ጨምሮ የፍርድ ቤቶችና የአዲስ አበባ  ከተማ መገናኛ ብዙሃንን የ5 ዓመት የስራ አፈጻጸም ገምግሞ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም