የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማህበር ለህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

82

ሐረር፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሐረር ለሚገኘው የሕይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከ250 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ዛሬ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ሕክምና እየሰጠ ለሚገኘው ሆስፒታል አገልግሎት የሚውል መሆኑን በማኅበሩ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ሥራአስኪያጅ አቶ አስፋው ሰንበቶ ገልጸዋል።

150 ፍራሽና ብርድ ልብስ፣ 75 ጥንድ አንሶላ፣ 75 የመሬት ምንጣፍ እንዲሁም ደረቅና ፈሳሽ ሣሙና ማኅበሩ ካደረገው ድጋፍ ውስጥ ይገኙበታል።

አቶ አስፋው ማኅበሩ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከክልሉ መንግሥት ጋር  እየሰራ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲልም ግምታቸው ከ400 ሺህ ብር በላይ የሚሆኑ የአልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች ለክልሉ ሀብት አሰባሰብ ዐብይ ኮሚቴ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።

የሆስፒታሉ ሥራአስኪያጅ ዶክተር ኢብሳ ሙሣ የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማኅበር ያደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ለሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ሌሎችም አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም