የአገሪቱን አረንጓዴ ልማት ዕቅድን ለማሳካት ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ይገባል

101

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዕቅድ ለማሳካት ችግኞችን መትከልና መንከባከብ እንደሚገባ የኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ከ350 በላይ የቢሮው አመራሮችና ሠራተኞች በዛሬው ዕለት  ከ2 ሺህ 4 መቶ  በላይ  ችግኞችን በሆለታ ከተማ  ተክለዋል፡፡

 ቀጣዩን ትውልድ ተጠቃሚ ለማድረግ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ እንደሚገባቸው በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በዚሁ ወቅት እንደገለጹትም የአረንጓዴ አሻራን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ ሁሉም ድርሻውን ሊወጣ ይገባል፡፡

''ዛሬ የሚተከሉት ችግኞች ለነገው ትውልድ ማረፊያ ናቸውና ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ችግኝ መትከል የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ስለሚረዳም እስከ ፍጻሜው ድረስ መንከባከብ ይገባል ብለዋል፡፡

ችግኞች ከመተከላቸው አስቀድመው ጉድጓድ ቢቆፈሩ፤ ችግኞችን የመጽደቅ አቅም እንደሚጨምረውም ጠቁመዋል፡፡

ሠራተኞችና አመራሮች ባለፈው ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ፤ችግኞቹ እስኪጸድቁ ድረስ ተመላልሰው የመንከባከብ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራም የመደበኛ ስራ አካል ይሆናል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

በችግኝ ተከላው ወቅት የተሳተፉ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየትም አረንጓዴ አሻራ በማሳረፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንደተወጡ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ቢሮ ሠራተኞች እንደመሆናቸውም መጠን ለሌሎች አርዓያ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡  

ችግኝ በመትከል የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

ለወደፊትም ዛሬ የተተከሉ ችግኞችን ተመላልሰው እንደሚንከባከቡም ተናግረዋል፡፡

ችግኖቹ ጸድቀው በራሳቸው ውሃ መሳብና ማበብ እስኪችሉ ድረስም ዘወትር የመንከባከብ ስራውን እንደሚወጡም ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በዚህ የክረምት ወቅት 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ይታወሳል፡፡

የዛሬው መርሐ ግብር የዚሁ አካል እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም