ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ግብዓት መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ

57

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

እስከ ዛሬ ሰኔ 20/2012 ዓ.ም ድረስም ግዢ የተፈፀመባቸውን እና በመጓጓዝ ሂደት ላይ ያሉትን ሳይጨምር ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ግምታቸው ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የህክምና ግብዓቶች ማሰባሰብ እና ማሰራጨት መቻሉን ገልጿል፡፡

ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው በመንግስት ሲሸፈን ቀሪው 40 በመቶ በተለያዩ አጋር አካላት የተሸፈነ ነው ተብሏል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እስካሁን ከተሰባሰቡት ግብዓቶች መካከል ከ513 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጪ ያላቸው የህክምና ግብዓቶች ወደ ክልል እና የተለያዩ ማዕከላት መሠራጨታቸውን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ ከዚህም የግል ደኅንነት መከላከያ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ከ13 ሚሊዮን ሊትር በላይ ኦክስጅን ማቅረብ የሚያስችሉ 3 ሺህ 600 የኦክስጅን ሲሊንደሮችን እና 1 ሺህ 100 በህሙማን ደም ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን ለመለካት የሚያስችሉ መሳሪያዎች ለክልሎች እና ለሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የህክምና ማዕከላት መሰራጨቱን ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡