መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለ900 ተማሪዎች የትምህርት መከታተያ ሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ ስልክ ድጋፍ አደረገ

176

መቀሌ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ትምህርታቸውን በሬዲዮ በመከታተል ላይ ለሚገኙ 900 ተማሪዎች የሬድዮ እና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ  ከ700ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ  500 ሬዲዮኖችና 400 ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች  ናቸው።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እንደገለጹት ድጋፉ በመቀበያ ችግር ምክንያት የሬድዮ ትምህርት ፕሮግራም መከታተል ላልቻሉ  ተማሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ድጋፉ የተደረገላቸው መቀሌን ጨምሮ በአምስት የክልሉ ወረዳዎች የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎች  እንደሆኑ አመልክተው በየቤታቸው ትምህርታቸውን በሬዲዮ ለመከታተል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግስት የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳይቋረጥ  እያደረገ ያለውን  ጥረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

ተማሪዎች በሬድዮ የሚተላለፍ ትምህርት በመከታተል ጥራትን ለማረጋገጥ  እንደሚረዳም ፕሮፌሰር ክንደያ አስረድተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ላልቻሉ ተማሪዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዓይደር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆነው የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ አይነስውሩ  አለም ተስፋዬ በሰጠው አስተያየት  የተደረገው ድጋፍ ከትምህርት ፕሮግራሙ በተጨማሪ ወቅታዊ የዓለማችን ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለን ነው ብሏል።

በተለይም ለአካል ጉዳተኞች የተለየ ድጋፍ ማድረግ ሰብአዊና ዜግነታዊ ኃላፊነት መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም