በጋምቤላ የባለሀብቶች ማህበር ኮሮናን ለመከላከል የሚረዳ የምግብ ድጋፍ አደረገ

58

ጋምቤላ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በግብርና የተሰማሩ አልሚ የባለሀብቶች ሁለገብ ማህበር የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲረዳ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።

የማህበሩ ሊቀመንበር አቶ ኡኩም ኦጃቶ በድጋፉ ርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ድጋፉን ያደረጉት ወረርሽኙ በህብረተሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንዲያግዝ ነው።

ጤናማ ማህበረሰብ በሌለበት የልማት ስራዎችን ማከናወን እንደማይቻል ጠቁመው የማህበሩ አባላት ይህንንም ግምት ውስጥ ማስገባት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ድጋፉ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት 807 ኩንታል በቆሎና ማሽላ የምግብ እህል መሆኑን አመልክተዋል።

ማህበሩ በቀጣይም ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ወረርሽኙን በመከላከሉ ረገድ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ድጋፍን ሲረከቡ እንደገለጹት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የኮሮና ወረርሽኝ በመከላከሉ ስራ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

በክልሉ ግብርና ዘርፍ  የተሰማሩ የአልሚ የባለሃብቶች ማህበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ ማህበሩ ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥል እምነታቸው መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ  ገልጸዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው የሃብት ማሰባሰብ መረሃ ግብር ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ  የክልሉ የገቢ አሰባሰቢ ግብር ኃይልና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ ናቸው።

እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ከርክክቡ በኋላም በጋምቤላ ከተማ አቶ ኃይሌ አዲስ በተባሉ  የማህበሩ አባል በ60 ሚሊዮን ተገንብቶ ስራ የጀመረው የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገብኝቷል።    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም