የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የድርድሩ ተግዳሮቶች

472

                                 ዳግም መርሻ (ኢዜአ)

ሰሞኑን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት በመቀጠል የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን አበይት አጀንዳ የሆነውና የህዝቡን ትኩረት እየሳበ የሚገኝ ጉዳይ ቢኖር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታና የድርድሩ ሂደት ነው። በአጀንዳው ዙሪያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ከግብጽና ከሱዳን ጋር እየተካሄደ ያለው ድርድር እንደ አባይ የፍሰት መጠን ከፍና ዝቅ የሚልና እልህ አስጨራሽ ነው።

የወንዞች ሁሉ አውራ ስለሆነው ዓባይና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የግድብ ግንባታ ብዙ ተብሏል፤ ብዙም ተጽፏል። ከናይል ወንዝ  86  በመቶ ውሀ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ ቀሪው 14 በመቶ ደግሞ ከነጭ አባይ የሚገኝ ነው ። ታዋቂው ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን “…አባይ አባይ…የሀገር አድባር…የውጭ ሲሳይ…” እያለ ቅኔ የተቀኘለት ዓባይ የኢትዮጵያን ለም አፈር ጠራርጎ እያጋዘ ለግብጽና ለሱዳን በረከት እንደሆነ ለዘመናት ፈሷል። ዓባይ ለግብፅ የባህላዊና ዘመናዊ የመስኖ ልማት ዋነኛ አውታር ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ነው። በዚህም ግብጽ የተለያዩ አትክልትና የፍራፍሬ ምርቶችን ከራሷ አልፎ ለአለም ገበያ እያቀረበች የውጭ ምንዛሪ ቋቷን እየሞላች ትገኛለች። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያዊው ግዮንን ተጠቅማ ሰው ሰራሽ ሀይቆችን ፈጥራ ከፍተኛ የዓሳ ምርት ታመርታለች፤ የቱሪስት መስእቦችም ባለቤት ነች ግብጽ።

በአንጸሩ አብዛኛው የሀገራችን አካባቢ በተለያዩ ምክንያት ተራቁቶ ለም አፈሩ በመከላቱ ሳቢያ በሚያጋጥመው የዝናብ እጥረት ለተደጋጋሚ ድርቅና ረሀብ ተጋላጭ እንድንሆን አድርጓል። ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነው ግብርናችንም ክፉኛ፤ እየተፈተነም ይገኛል። ለምሳሌ በ1970ዎቹ በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ አገሪቷ በታሪኳ ካጋጠሟት ሁሉ የከፋው ረሀብ ተከስቶ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአብራኮቿ ክፋዮች በረሀብ አለንጋ ተገርፈው ነገን እንደናፈቁ እንደዋዛ እስከ ወዲያኛው አልፈዋል። ክስተቱም እናት ኢትዮጵያን የድርቅና የረሀብ ተምሳሌት ሆና በመዝገበ ቃላት ጭምር እንድትጠቀስ አድርጎ ታሪክ ጠባሳውን ጥሎ አልፏል። ይሄው የ1977ቱ ረሀብ። ያኔ ኢትዮጵያውያን ከእጅ ወደ አፍ የሚበሉት አጥተው መመጽወትን እንጂ ምጽዋትን ለመቀበል የማይዘረጋው እጃቸው ለልመና ተዘርግቶ ሲማጸኑ ፤ ግብጻውያን የውሃ እጥረት ቢያጋጥማቸውም ቅሉ እንደ ኢትዮጵያ የከፋ የረሀብ አደጋ ሰለባ አልሆኑም። ከዚያ ዘመን በኋላም በአለም የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ኢትዮጵያውያን ለምግብ እህል እጥረት ሲዳረጉ፤ ግብጽ ምናልባትም እዚህ ግባ የማይባል የውሃ እጥረት ቢያጋጥማትም እንደ ኢትዮጵያ ስትራብ፣ ስትታረዝና እርዳታ ስትጠይቅ አልታየችም። ለዚህ ደግሞ አስቀድመው በዓባይ/ናይል ወንዝ ላይ የገነቧቸው በርካታ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችና የአስዋን ግድብ ከአደጋው እንደታደጓቸው  ይነገራል።

ኢትዮጵያ በ1977 ካጋጠመው አስከፊ ድርቅና ረሀብ በተጨማሪ በየ 10 ዓመቱ በተደጋጋሚ ድርቅ ተጠቅታለች። በርካታ ዜጎች የረሀብ ሰለባ ከመሆናቸውም በላይ ለምግብ እርዳታ ጥገኛ /ተመጽዋች ሆነዋል። ለዚህ ትልቁ ምክንያት ደግሞ ለግብጽ እንደ ገጸ በረከት የሚቆጠረውና በጉያዋ ያለው አባይ ለሀይል ማመንጫ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለአሳ እርባታ፣ ለቱሪዝም መስህብ ጥቅም ላይ አለመዋሉ ነው። በተፈጥሮ ሀብታችን በሆነው በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ሙሉ ተፈጥሯዊም ህጋዊም መብት ቢኖረንም በውስጣዊ አቅም ውስንነትና ውጫዊ ተጽእኖዎች ምክንያት ዓባይን አልምተን መጠቀም ባለመቻላችን ህይወታችንን በከፋ ድህነትና ጉስቁልና ስንመራ ኖረናል።

ዓለም በቴክኖሎጂ ርቆ በሄደበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከግማሽ በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የኤሌክትሪክ መብራት እንደናፈቀው ነው። በተለይ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውና በገጠር የሚኖረው ህዝብ እንዲሁም ከከተማ ነዋሪዎች አብዛኞቹ በኩራዝና በሻማ ጭስ እየተጨናበሱና በንጹህ መጠጥ ውሀ እጦት እየተሰቃዩ ጎስቋላ ኑሮ የሚመሩ ናቸው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ቢኖራትም ለዘመናት የበይ ተመልካች ሆና ኖራለች። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ዓባይ ከሀገሩ ይልቅ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ሲሳይ መሆኑ ነው። 

የናይል ተፋሰስ 11 ሀገራትን የሚያካልል ቢሆንም በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል ፍትሀዊ የውሀ አጠቃቀም ባለመኖሩ የወንዙን ውሀ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሲጠቀሙ የነበሩት ግብጽና ሱዳን ናቸው። እነዚህ ሀገሮች የላይኛውን የተፋሰሱ ሀገሮች ከግምት ውስጥ ያላስገቡና ያላሳተፉ ስምምነቶችን እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 ተፈራርመው በወንዙ ላይ ኢ-ፍትሀዊ  ተጠቃሚነትን እንግሰው ኖረዋል። በግብጽና በብሪታንያ መካከል የተካሄደው የ1929 የቅኝ ግዛት ስምምነት በወንዙ ላይ ለግብጽ ሙሉ የመጠቀም መብት የሚሰጥ ሲሆን፣ በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚገነቡ እና የግብጽን የውሀ ድርሻ የሚጎዱ ማንኛውም የግድብ እና የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ ውሳኔ የማሳለፍ መብት እንዳላት የሚደነግግ ነበር። በመቀጠለም እ.አ.አ. በ1959 የመጀመሪያውን ስምምነት መነሻ በማድረግ ግብጽና ሱዳን የተፈራረሙት ስምምነት በአመት 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ውሀ ማለትም 66 በመቶ  ለግብጽ፣ 18 ነጥብ 5 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ውሀ ማለትም 22 በመቶ ለሱዳን ድርሻ ደልድሎ ያስቀመጠ ነበር።

ግብጽና ሱዳን ስምምነቶቹን ሲያደርጉ በሚያስገርም ሁኔታ የዓባይ ውሀ ዋነኛ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን አላሳተፉም፤ ከነአካቴው ይመለከታታል ብለው አልቆጠሩም። እነዚህ ስምምነቶች በታችኛውና በላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያስገኙት ውጤት ቢኖር ጭቅጭቅንና አለመተማመንን ማስፋት ነው።

ግብጽ እነዚህን ስምምነቶች መሰረት አድርጋ ዓባይን ያለአንዳች ሀይ ባይ መጠቀም “ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብቴ ነው”፤ የሚለውን ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰቧን ለማሳካት ለነደፈችው ስልት፤ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ግብጽ ከአለም ባንክና ከሌሎች የገንዘብ አበዳሪ ተቋማት የነበራትን ግኑኝነት ተጠቅማ ኢትዮጵያ ብድር አግኝታ ዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እንዳትገነባና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ አድርጋለች። ግብጻውያን ተሰሚነትን ለማግኘት “ብቸኛው የህልውናችንና ሀገራዊ ደህንነታችን መሰረት የአባይ ውሀ ነው”…. “ኢትዮጵያ ለአረብ ሀገራትና ለእስልምና ሀይማኖት ጥሩ አመለካከት የላትም”… “ቀጣዩ የአለም ጦርነት መነሻው  ውሀ  ነው”…ወዘተ የሚሉ ሀሰተኛ ትርክቶችን በመንዛት የአረብ ሊግንና የመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሀገሮችን ለጊዜውም ቢሆን ከጎኗ ማሰለፍ የቻለች ሲሆን፣ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሀገሮችም ለግብጽ ፍላጎት ተገዥ እንዲሆኑ እየተሯሯጠች ትገኛለች።

በሌላም በኩል ቤተ-እምነቶችንና የሀይማኖት ተቋማትን በመጠቀም በዓባይ ውሀ ያለገደብ የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት ብዙ ተግታለች፤ ምንም እንኳን በምታስበው ልክ ባይፈይድላትም ዛሬም ከዚህ አድራጎቷ እንዳልተገታች የሰሞንኛው ላይ ታች መባዘንዋ ለዚህ አብነት ነው። ይህ አልሳካ ሲላት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች ናቸው ብላ የምታስባቸውን ስብስቦች በመደገፍ የኢትዮጵያን የልማትና የእድገት ጉዞ ለማደናቀፍ እየሰራች እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ደግነቱ ትናንት ዛሬ አይደለም!  የአባይን ውሀ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መርህ በፈጠረው ግፊት ምክንያት በተፋሰሱ ሀገሮች መካከል አዲስ ምእራፍ የከፈተውና ከኢትዮጵያ የትብብር አቋም የመነጨው ”የኢንቴቤ ስምምነት“ የናይል ተፋሰስ ሀገራት የትብብር ማእቀፍ (Nile Basine Cooperatve Framework Agreement) እ.አ.አ በ2011 እውን ለመሆን በቅቷል። ማእቀፉ የናይል ተፋሰስ በእኩልነትና በዘላቂነት ለማልማት እና ለማስተዳደር ያለመና ለፍትሀዊና ለምክንያታዊ የናይል ውሀ አጠቃቀም ፈር የሚቀድ ስምምነት በመሆኑ በላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም በኢትዮጵያ እንደ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ይቆጠራል። ስምምነቱን ኢትዮጵያ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያና ብሩንዲ የፈረሙ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳና ታንዛንያ ደግሞ ስምምነቱን ከመፈረምም አልፈው የሀገራቸው የህግ አካል አድርገውታል፡፡ ለአባይ ውሀ ምንም የውሃ ጠብታ አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው ውሀውን በቅኝ ግዛት ውል መሰረት ለብቻቸው መጠቀም የሚፈልጉት ግብጽና ሱዳን ደግሞ ስምምነቱ በውሀው ሀብት ላይ ማንም ሀገር ፈቃጅም ከልካይም ሊሆን እንደማይችል ስለሚያስቀምጥ ማእቀፉን አልፈረሙም፤አላጸደቁም። 

ኢትዮጵያ በትብብር ስምምነቱ ማዕቀፍ መሰረት ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር የድርድሩን ሂደት በአንድ ጎን እያስኬደች በሌላ በኩል የአባይ ወንዝን ማልማት ከድህነት የመውጣት ወይም ያለመውጣት ጉዳይ መሆኑ ታምኖበት እናት ምድሩን አልምቶ ወገኑን እንዲጠቅም ታልሞ በወርሀ መጋቢት በ2003 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተጀምሮ አሁን ላይ ግንባታው 74 በመቶ ላይ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የግድቡ ስራ በግብጽም ሆነ በሱዳን የውሀ ድርሻ ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያደርስ ጥናቶችን ዋቢ አድርጋ እየገለጸች ትገኛለች። ከዚህ ባሻገርም ከሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች (ከሱዳንና ግብጽ)  ጋር ለመደራደር ሁልግዜም ዝግጁ እንደሆነች ነው፤ ለአፍታ እንኳን አቅማምታ አታውቅም።  የሆነው ሆኖ  ግብጽ ‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት -- ነውና ቅሉ › የህዳሴን ግድብ አስመልክቶ አባይ “የኔ ብቻ ይሁን” በሚለው ያረጀና ያፈጀ  አስተሳሰቧ ላይ ተጣብቃ ሲያሻት የክተት ነጋሪት በቀጥታ በሚሰራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዋ በመጎሰም፣ ሲያሻት ደግሞ የውሀው 86 በመቶ ባለድርሻ የሆነችው ኢትዮጵያን ያገለሉትን የ1929ኙን እና የ1959ኙን ቅኝ ግዛት ውሎች እየመዘዘች፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግማሽ ልቧ ልደራደር እያለች እዚህ ደርሳለች።  በዚህ ላይ የግብጽና የሱዳን የአቋም መዋዠቅና  የፖለቲካዊ  ትርፍን የማስላት አካሄድ የድርድር ሂደቶቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ ሀገሮች በሚፈልጉት መልኩ ውጤታማ እንዳይሆኑ  አድርጓል።

ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እውን መሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፣ ከደሀ እሰከ ሀብታም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ እያደረጉም ነው። ይህም ሆኖ ግን ግድቡ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች በተያዘለት መርሀ ግብር መሰረት መጠናቀቅ አልቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት  “የግድቡ ግንባታ አንድ አመት በዘገየ ቁጥር አንድ ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እያደረሰ ነበር። ሀገሪቷ እስካሁንም ማግኘት የነበረባትን ስድስት ቢሊዮን ዶላር አጥታለች” ብለው ነበር።

ከሁሉም በላይ በዚህ ሰአት ትልቅ ፈተና ሆኖ የሚገኘው የታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች በተለይም የግብጽ ተለዋዋጭ ባህሪ ነው። ለዚህም ሰሞነኛው ዲፕሎማሲያዊ እሰጣ ገባ ማሳያ ነው። ግብጽ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውስጣዊ መረጋጋት ባጣሁበት ጊዜ የተጀመረ ግድብ ነው። አሁን በተሻለ ሁኔታ ላይ ስለምንገኝ ኢትዮጵያ ግድቡን ከዳር እንዳታደርስ ማድረግ አለብኝ” የሚል አቋም መያዟ በሚደረጉት ድርድሮች ላይ ሶስቱ ሀገራት የተፈራረሙትን የ2015ቱን የመርሆች ስምምነት በሚጻረር መልኩ ጋሬጣ ሆኗል።

 ‹አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀማው› እንዲሉ ግብጽ በተለይ ከሁለት አመት ወዲህ በሀገራችን እዚያም እዚህ ሲከሰቱ የነበሩ አለመረጋጋቶችንና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ እሰጣ ገባዎችን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ቀድም ሲል ሶስቱ ሀገራት ያካሂዱትን ውይይት ገፍታ ወደ አሜሪካ እና የአለም ባንክ አደራዳሪነት በመወስድ ራሷ ያዘጋጀችውን የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ እንድትፈርምና ይህም ሳይፈረም የግድቡ ውሀ ሙሌት እንዳይጀምር በአሜሪካ በኩል ተጽእኖ ለማሳደር ሞክራለች። ምንም እንኳን የአሜሪካ ትቁር አባላት ስብስብና የቀድሞ ታዋቂ አሜሪካውያን ባለስልጣናት የአሜሪካንን አቋምና ድርጊት አትብቀው ቢተቹም። ይባስ ብሎም ግብጽ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ አጋርና ስለግድቡ ጠቃሚነት አስረግጣ ስትናገር የነበረችውን ሱዳንንም  የአቋም መዋዠቅ ውስጥ እንድትገባና አቋሟን በየጊዜው እንድትቀያር ትልቅ ደባ በመስራት ላይ ነች።

ግብጽ የህዳሴው ግድብ የውሀ ሙሌት እንዳይጀምር ከወዲሁ ቁጭ ብድግ እያለች፤ ከታች ላይ ብትባዝንም “ኢትዮጵያውያን የግድቡን የመጀመሪያ የውሀ ሙሌት በመጪው ሀምሌ ወር ለመጀመር የማንንም ፈቃድ አያስፈልገንም” ብለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል ተረጋግጯል። ግድቡ በተያዘለት እቅድ መሰረት ሙሌቱን ለመጀመርም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

በድጋሚ በሱዳን አነሳሽነት ሶሰት ታዛቢዎች (በአሜሪካ፣ በአውሮፓ ህብረትና በደቡብ አፍሪካ) በተገኙበት ተቋርጦ የነበረው የሶስቱ ሀገሮች ድርድር ተጀምሮ ለቀናት ተካሂዷል። በድርድሩም በመሰረታዊ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት የደረሱ ቢሆንም፤ ህግ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ በሚያስችሉ የህግ ጉዳዮች ላይ ግን እንደሚቀራቸው፤ በእስካሁኑ የድርድር ሂደት ሱዳን ተጨማሪ ምክር እንደምትፈልግ መግለጿን ተከትሎ ድርድሩ ከዚያ በኋላ እንደሚቀጥል ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ከዚህ የድርድር ሂደት ጎን ለጎን  ግብጽ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጫና ለማሳረፍ ለሁለተኛ ጊዜ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጥያቄ አቅርባ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያሳልፍ ግፊት ብታደርግም ምክር ቤቱ ሀገራቱ ልዩነታቸውን በጋራ እንዲፈቱ “እዛው ጨርሱ” አይነት ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

በተመሳሳይም የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ግብጽ የህዳሴ ግድብ ጉዳይን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መውሰዷን እንዲሁም በወንዙ ላይ የተፈጥሮ መብት እንዳላት እንዲደግፉ የውሳኔ ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን የውሳኔ ሀሳቡን ግን ጅቡቲ፣ ሶማሊያና ኳታር ተቃውመዋል።

ይህ እንዳለ ሆኖ በውይቱ ላይ ከታዛቢነት ውጪ ሌላ ሚና እንደሌላት የተነገረላት አሜሪካ በብሄራዊ ምክር ቤቷ በኩል በተለቀቀ ቲውተር መግለጫ ውይይቱን የሚያደፈርስ እና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚዳፈር ማስጠንቀቂያ ቢጤ መግለጫ ሰጥታለች። የመግለጫው ፍሬ ሀሳብ በአጭሩ “የሁሉንም ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስምምነት ሳይደረግ የውሀ ሙሌት መደረግ የለበትም” የሚል ነበር። ይህ መግለጫ የሚያሳው ነገር ቢኖር ለግደቡ ግንባታ ድንቡሎ ሳንቲም ያላበደረችው የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ግብጽ በእንግሊዝ በተፈረመው የቅኝ ግዛት ውል መሰረት ብቸኛ የአባይ ውሀ ተጠቃሚ እንድትሆን ድብቅ ሴራ እየጠነሰሰች መሆኑን ነው።

ምንም እንኳን የአሜረካንን ሚናና የያዘችውን አቋም ተገቢና ሚዛናዊ እንዳልሆነ የተለያዩ ታዋቂና ተሰሚነት ያላቸው አሜሪካውያን ለምሳሌ የጥቁሮች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን ፣ የጥቁር አሜሪካውያን ኮንግሬስ አባላት ስብስብ እንዲሁም እንደ ሱሳን ራይስ፣ ጄንዳይ ፍሬዘር ሄርማን ኮህን አይነት የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኞች ቢተቹትም የአሜሪካ ድርጊት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚዳፈር ከመሆኑም በላይ ለአለም ህዝቦች መብትና ፍትህ መረጋገጥ ጥብቅና እቆማለሁ ከሚል ሀገር የማይጠበቅ መሆኑን ዘገባዎች አመላክተዋል። እነዚህ አካላት ያልተረዱት ነገር ቢኖር ለግብጽ ስጦታ የሆነው አባይ ለኢትዮጵያ እርግማን መሆን እንደማይችል ነው።

ግብጽ ከምታሳየው ተለዋዋጭና መርህ አልባ እንቅስቃሴዋ አንጸር የሚደረጉት ድርድሮች ፍሬ ያፈራሉ ብሎ ለማመን ያዳግታል። ምክንያቱም ግብጽ ለይስሙላ ለድርድር እንቀመጥ እያለች ዋና ትኩረቷ በሚቻላት ሁሉ የውሀ ሙሌቱን ከቻለች ማስቆም ካልሆነላት ደግሞ ማዘግየት ነውና። ስለዚህም ግብጽን ለመመከት የሚያስችል ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነቱን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። በዓባይ ላይ ያለንን ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብት ለማስከበርና ለማስጠበቅ ሁላችንም በሙሉ አቅማችን ተግተን መስራት ይጠበቅብና። 

ከዚህ አኳያ ከአምባሳደሮቻችንና ከዲፕሎማቶቻችን፣ ከፓርላማ አባላት፣ ከጋዜጠኞች፣ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ከምሁራን በአጠቃላይ ከእያንዳንዱ ዜጋ ብዙ ስራ ይጠበቃል። ለዚህም ኢትዮጵያ ባልተስማማችበትና ባልፈረመችው የቅኝ ግዛት ውል መገዛት ከሞራልም ሆነ ከአለም አቀፍ ህግ አኳያ ተቀባይነት እንደሌለው፣ ግብጽ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየነገረች ያለችው ሀሰት መሆኑን፣ የግድቡ ግንባታ ለኢትዮጵያውያን ያለውን ኢኮናሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ፣ የግድቡ ግንባታ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገሮች ጉዳት እንደሌለው…..ወዘተ እውቀትን መሰረት ባደረገና በተደራጀ ሁኔታ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳትና በዲፕሎማሲ ስራ መጠመድ ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ግን ለግብጽ ትልቅ ምላሽ የሚሆነው ግድቡን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብና መርሃ ግብር መሰረት የመጀመሪያውን የውሀ ሙሌት በማካሄድ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቶ ዓባይን በዋናነት የኢትዮጵያውያን ብሎም የጎረቤት ሀገሮች የብርሀን ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ሰላም !

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም