የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመምህራን ቤት መስሪያ 12 ሄክታር መሬት ማከፋፈል ጀመረ

52

ድሬዳዋ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የመምህራን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ ለመመለስ ያዘጋጀውን  12 ሄክታር መሬት ለተደረጁ ማህበራት ማከፋፈል ጀመረ።

የተዘጋጀውን የቦታ ፕላን  የማስረከብ ስነስርዓት ትናንት በጀመረበት  ወቅት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃርና ሌሎች የአስተዳደሩ አመራሮች  ተገኝተዋል።

ርክክቡ ሲካሄድ የአስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደራራ ሁቃ እንደተናገሩት ሌሎቹም መምህራን ተደራጅተውና አስፈላጊውን  መስፈርት አሟልተው በመጡበት ወቅት ቦታው ይሰጣቸዋል።

ከመምህራኑ በተጨማሪ ለ6ሺህ  ቤተሰቦች ሁለት  መቶ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ተዘጋጅቶ በቀጣይ አስር  ቀናት በዕጣ ይከፋፈላል ብለዋል፡፡

መምህራን የሀገሪቱን ጅምር የብልጽግና ጉዞ ዳር  በማድረስ በኩል የማይተካ ሚና  እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ የአስተዳደሩ  ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ ናቸው።

ይህን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለሚያቀርቡት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ መስጠት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት መምህር አበበ ታምራት ፤ የመምህራን የዓመታት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የተደረገው ጥረት ፍሬ ማፍራቱ መምህራን የተጣለባቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ  ለማሳካት ያግዛል ብለዋል፡፡

አስተዳደሩ ያዘጋጀውን 12 ሄክታር መሬት ለማከፋፈል  48 ማህበራት ቢደራጁም የሚጠበቀው የቁጠባ ገንዘብ አሟልተው ለጨረሱ  የመምህራን ማህበራት መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

የቦታ ፕላን ከተረከቡት ማህበራት አስተባባሪዎች መካከል መምህር ዘላለም አዱኛ በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄያቸው ምላሽ  እንዲያገኝ ትኩረት መሰጠቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም መደሰታቸውንና በወሰዱት ቦታ ላይ በፍጥነት ቤት ገንብተው ለሌሎች መምህራን አርአያ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም