በአዳማ ከተማ የተገነቡ 62 ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ተዘጋጁ

50

አዳማ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) አዳማ ከተማ 764 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነቡ 62 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለህብረተሰቡ አገልግሎት ተዘጋጁ።

ፕሮጀክቶቹ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።

በምረቃው ስነስርዓት ወቅት የአዳማ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ደሜ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ የከተማዋ ህብረተሰብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በልዩ ትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ግንባታቸው ሳይጠናቀቅና የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ቅሬታ ሆነው የቆዩት ጨምሮ 62 የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ከፍጻሜ በማድረስ ለአገልግሎት ማዘጋጀት እንደቻሉ አስታውቀዋል።

ከፕሮጀክቶቹም መካከል አዳዲስ የአስፓልትና ድንጋይ ንጣፍ መንገድ ፣ 38 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥና የዋና መስመሮች የመብራት ዝርጋታና የጎርፍ መውረጃ ቦዮች ይገኙበታል፤

እንዲሁም ድልድዮች፣ የጠጠርና ነባር አስፓልት መንገድ ጥገና ፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያ ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ማምረቻና መሸጫም ተጠናቀው ለአገልግሎት ከተዘጋጁት ውስጥ የተጠቀሱት ፕሮጀክቶች  ናቸው።

አስተዳደሩ ለልማት ፕሮጀክቶች 764 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለዓመታት በመጓተት የህዝብ ቅሬታ ፈጥረው የነበሩ 16 ፕሮጀክቶች ፣ 38 አዳዲስና 8 ጥገና የተደረገላቸው ጨምሮ 62 ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት  መዘጋጀታቸውን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።

በተጨማሪ አስተዳደሩ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል በማህበር ለተደራጁ 9ሺህ 509 ለሚሆኑ የመንግስት ሠራተኞችና ነዋሪዎች የቤት መስሪያ ቦታ ካርታ አስረክበዋል።

በአዳማ ከተማና አካባቢዋ  ወደ ባለሀብትነት  ለተሸጋገሩ አርሶ አደሮች የኢንቨስትመንት መሬት ተሰጥቷል።

ለዘመናት ያለይዞታ ማረጋገጫ የቆዩ ለተለያዩ ቤተ እምነቶች የይዞታ ባለቤትነት ካርታ አገኝተዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የህብረተሰቡን የመልማትና የተጠቃሚነት ፍላጎት ለማሟላት የለውጥ ኃይሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ በትኩረት መስራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ከተሞች በቂ እና ወቅቱን ያገናዘበ መሰረተ ልማት እንዲኖር መንግስት ስትራቴጂ በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱን አስረድተዋል።

አቶ ሽመልስ በበጀት ዓመቱ  የተለያዩ ማነቆዎች በማለፍ የህዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያግዙ ውጤታማ ስራዎች መከወናቸውን ገልጸዋል።

"የልማት ጥያቄዎች መመለስ የክልሉ ግንባር ቀደም አጀንዳ ነው"  ያሉት ፕሬዝዳንቱ  መንግስት የህዝብ ቅሬታዎችን ፈትሾ  በመለየት በሁሉም የክልሉ ዞኖች፣ ከተሞችና ወረዳዎች ልማቱን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የከተማዋን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት 2 ቢሊዮን 600 ሚሊዮን በጀት ግንባታ ለማስጀመር ዛሬ የመሰረት ድንጋይ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት በክልሉ ከተሞችና ወረዳዎች ከ12 ሚሊዮን  በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ 4ሺህ  የሚጠጉ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ቀደም ሲል ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም