የአማራና አፋር ህዝቦች ልማትና ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሁሉቱ ርዕሳነ መስተደድሮች አስታወቁ

66

ደሴ፣ ሰኔ20/2012 የአማራና አፋር ወንድማማች ህዝቦችን ልማትና ሰላማዊ ግንኙነት በማጠናከር የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች አስታወቁ።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሲካሄድ የቆየው የሁለቱ ክልሎች  አመራሮች ውይይት ትናንት ማምሻውን ተጠናቀቀ፡፡

 በውይይቱ ማጠናቀቂያ ወቅት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት አማራና አፋር  የማይለያዩ የጋራ ባህልና እሴቶቻቸውን ጠብቀው ለዘመናት የዘለቁ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፡፡

ሆኖም  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋራ ለማልማት ጥሩ አጋጣሚ እንጂ ወደ ግጭት በማይወስዱ የጋራ ሃብቶችን ምክንያት በማድረግ ሁለቱን ህዝቦች ለማበጣበጥ የሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች መኖራቸው ተደርሶበታል ብለዋል።

እነዚህ የሰላምና ልማት እንቅፋቶችን  የሁለቱም ክልል ህዝቦች አጋልጠው እንዲሰጡ በማድረግ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ  በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥርው በህግ ቁጥጥር ስር ያሉ መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

አልፎ አልፎ ከግጦሽ፣ እርሻ መሬትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ  የሚስተዋሉት ችግሮች አመራሩ ተከታትሉ  የመፍታት ቁርጠኝነትና ቸልተኝነት የተፈጠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር በኃላፊነት እንዲሰራ ከመደገፍ ጎን ለጎን ሆን ብለው የሚያጠፉም ወደ ተጠያቂነት ለማምጣት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡

አካባቢው ሰላም ውሎ እንዳያድርና የተጀመሩ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እንዲሻክሩ የሚሳሩ ኃይሎችን በመለየትም የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በሁለቱ ክልሎች  የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር አዋሳኝ አካባቢዎችን በማልማትና መሰረተ ልማቶችን በማሟላት በቀላሉ እንዲገናኙና ማህበራዊ ትስስራቸውን እንዲያጎለብቱ እንደሚደረግም አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀው ግንኙነትና  ባህላዊ  እሴቶች እንዲጎለብቱ በየደረጀው የሚደረጉ ውይይቶች ለውጥ በማምጣታቸው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ በሰመራና ኮምቦልቻ በተካሄዱ መድረኮች ክፍተቶች እንዲታረሙ፣ ጥንካሬዎች ደግሞ እንዲቀጥሉ  አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

ሁለቱን ህዝቦች ለማቃቃር በሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች ላይም የእርምት እርምጃ በመውሰድና ቀጠናውን ሰላም በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲከበር ይደረጋል ብለዋል፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጻ አፋር ከአማራ ጋር በ13 ወረዳዎች  እንደሚዋሰን አመልክተው ከእነዚህም በአምስት ወረዳዎች ላይ ብቻ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ ስለ ግጭትና ሰላም ሳይሆን የዕለት ተዕለት ጥያቄያቸው አዋሳኝ አካባቢዎች እንዴት ለምተው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራቸውን ማጎልበት እንዳለባቸው ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሰላምና  አብሮነት ሞዴል ወረዳዎችን ተሞክሮ በማስፋት ሁሉም በጋራ የሚለሙበትን መንገድ በጋራ የማመቻቸት ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለፖለቲካ ጥቅመኞችና የጥፋት ኃይሎች ሳይታለሉ የጥንቱ አብሮነት፣ ሰላምና ባህላዊ  እሴቶቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አቶ አወል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የሰሜን ዕዝ መከላከያ ስራዊት ዋና አዛዥ ሌትናል ጀነራል ድሪባ መኮንን  በሰጡት አስተያየት "ህብረተሰቡ የየአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የፀጥታ ኃይሉን ጫና ማቃለል አለበት" ብለዋል፡፡

መከላከያ ስራዊቱ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ከውጭ ጠላት  መጠበቅ እንጂ በማይለያዩ ወንድማማቾች ህዝቦች  በቀላል አለመግባባቶች ላይ ጊዜውን ማጥፋት እንደሌለበት ተናግረዋል።

ስራዊቱ ከመቼውም በላይ አቅሙን አጎልብቶ የህዝቡንና  የሀገርን  ደህንነት ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በውይይቱ ከሁለቱም ክልሉች  የተወጣጡ  የስራ ኃላፊዎች ፣ የፀጥታ አካላት፣ የሰሜን ዕዝ መከላከያ ስራዊት አመራሮችና አባላት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም