የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ቡድን ዱከም ላይ ችግኝ ተከለ

97

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ቡድን በዱከም ከተማ የችግኝ ተከላና የኮቪድ-19 መከላከል ላይ ኅብረተሰቡን የማነቃቃትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አከናወነ።

አርቲስት ሠራዊት ፍቅሬን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች “ዱከምን  እንቃኛት”  የሚል መርሃ  ግብር  በማዘጋጀት የተለያዩ ተግባራት አከናውነዋል። 

ለኢዜአ አስተያየት የሰጠው የቡድኑ መሪ  አርቲስት ሠራዊት  ፍቅሬ እንዳለው  ኮቪድ-19  እንዳይስፋፋ  በርካታ  ተከታይ ያላቸው አርቲስቶች ግንዛቤ በመፍጠር አርዓያነታቸውን አሳይተዋል።

“አርቲስቶች ከሕዝብ የወጣንና የሕዝብ ልጆች እንደመሆናችን ኅብረተሰቡ ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን ተወጥተናል” ብሏል።

በሁለተኛው አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ  ግብር መሳተፋችን የጠቅላይ  ሚኒስትር አብይ አህመድን  ጥሪ  መቀበላችንን ያመለክታል ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።

አርቲስት ሠራዊት ዛሬ የተከልናቸውን ችግኞች  ተመላልሰን የመንከባከብና  እንዲፀድቁ  የማድረግ  ሃላፊነታችንንም  እንወጣለን ነው ያለው።

አርቲስት ታደለ ሮባ በበኩሉ ዱከም የኢንዱስትሪ ማዕከል በመሆኗ ከኢንዱስትሪዎች  የሚወጣው ጭስ  ተፈጥሮ  ላይ  የሚያደርሰውን ተፅእኖ የሚከላከል ችግኝ በመትከሉ መደሰቱን ተናግሯል።

አርቲስቶች በኪነ-ጥበብ ስራቸው ብቻ ሳይሆን ከኅብረተሰቡ ጋር  በአካል በመገናኘት ስለ  ኮቪድ-19  አስከፊነት  ግንዛቤ መስጠታቸው የሕዝብ ልጅ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ሲልም አክሏል።

የችግኝ ተከላና ግንዛቤ የማስጨበጥ መርሃ ግብር በሌሎች የአገሪቷ ከተሞች ለማካሄድ ማቀዳቸውንም ጠቁሟል።

“ችግኝ መትከል የአየር ብክለትን ለመከላከል ስለሚረዳ እኛም በዚህ አገራዊ ጥሪ በመሳተፋችን ለዘርፉ አስተዋጽኦ እንዳበረከትን ይሰማናል” ያለችው ደግሞ አርቲስት ገነት ንጋቱ ነች።

ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የእነርሱን አርዓያ በመከተል በሚኖርበት አካባቢ ችግኝ እንዲተክልም አሳስባለች።

የዱከም ከተማ ከንቲባ አቶ ተሾመ ግርማም “በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው የኪነ-ጥበብ  ባለሙያዎች  ይህን  በማድረጋቸው የዜግነት ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል” ብለዋል።

በከተማዋ 2 ሚሊዮን ችግኖች ለመትከል መታቀዱን የገለጹት ከንቲባው አርቲስቶቹ ችግኝ መትከላቸው ዕቅዱን በቀላሉ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ዱከም የኢንዱስትሪ ከተማ እንደመሆኗ የኮሮናቫይረስ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ያነሱት አቶ ግርማ አርቲስቶቹ የፈጠሩት ግንዛቤ ኅብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ ያስችላል ብለዋል።

ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የአርቲስቶቹን አርዓያ መከተል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የአርቲስቶቹ ቡድን በዱከም ከተማ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች የሚውል የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍም አበርክቷል።