በሃዲያ ዞን በ464 ሚሊዮን ብር ወጪ አደጋ የመከላከል ስራ ተከናወነ

69

ሆሳዕና ሰኔ 19/2012 (ኢዜአ)  በሀድያ ዞን የተፈጥሮ አደጋ ለመከላከልና ተፈናቃይ ወገኖችን ለመታደግ በ464 ሚሊዮን ብር ወጪ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት ገለፀ።

በጽህፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ በቀለ ጡሜቦ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት 78 የገጠር ቀበሌዎች ላይ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በ9 ሺህ ሔክታር መሬት  ላይ የነበረ ቋሚና ጊዜያዊ ሰብል ወድሟል።

በዚህም ከ84 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመፈናቀል ለምግብ አቅርቦት ችግር የተዳረጉ ሲሆን 57 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በሚገመት ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል።

የተፈናቃሉ ወገኖችን ወደ ተዳፋታማ ቦታዎች እንዲሰፍሩ በማድረግ በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ትብበር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የጎርፍ ተጠቂ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት 152 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታና የጎርፍ መቀልበሻ ስራ ተከናውኖ ለአገልግሎት መብቃቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩን በማሳተፍና አስፈላጊውን የቁሳቁስ ግብዓት በማቅረብ ከ42 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የድንጋይና የአፈር እርከን ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የግብርና ስራዎችን አስተሳስሮ በማስቀጠል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም አቶ በቀለ አብራርተዋል።

 በዞኑ ሻሰጎ ወረዳ ሁርበጫ አንጣጣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ማቲዎስ ባፌ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው ተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ በመከሰቱ ከቤት ንብረታቸው ከመፈናቀላቸው ባለፈ የዘሩት አዝርዕት በጎርፍ በመወሰዱ ለችግር ተዳርገዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ኑሮአቸውን በመምራት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ክረምት በገባ ቁጥር የስጋት ኑሮ እንደሚገፉ የተናገሩት ደግሞ  በምስራቅ ባደዋቾ ወረዳ  ቆርጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ከበደ አዴቦ ናቸው።

ከተረጂነት በመውጣት ኑሮአቸውን በአግባቡ ለመምራት ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ከበደ መንግስት በሚያደርገው ጥረት ውስጥም የመፍትሄ  አካል  ለመሆን ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም