የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ የሞከሩ ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር በከፈቱት ተኩስ ሞትና ጉዳት ደረሰባቸው

85

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) በቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ላይ የጸጥታ አካላትን አልባሳት በመጠቀም የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ የሞከሩ ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር በከፈቱት ተኩስ ሞትና ጉዳት ደረሰ።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ የቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ የሞከሩ ስምንት ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር ተኩስ ከፍተው ነው ሞትና ጉዳት የደረሰው።

ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ኢንተለጀንስ አባላት ክትትል እየተደረገባቸው ሳለ ወደ ቻይናዊያኑ ቅጥር ግቢ መግባታቸውን ነው የተገለፀው።

ዘረፋውን ፈጽመው ሲወጡ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢጠየቁም ተኩስ በመክፈታቸው በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሊያመልጡ ከሞከሩ ሁለት ግለሰቦች የአንዱ ህይወት ሲያልፍ ሌላኛው ቆስሎ ለህክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዱ፤ ስድስቱ ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ግለሰቦቹ ቀደም ሲልም የተለያዩ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብሶች በመልበስ እና የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እንዲሁም የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም በተለያዩ ስፍራዎች የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈጽሙ እንደቆዩ አስታውሷል።

ይህንንም ከህብረተሰቡ በተለያዩ ጊዜ የደረሱ ጥቆማዎች እንደሚያመለክቱ፤ በዛሬው ዕለትም በተለመደው ሁኔታ የወንጀል ድርጊት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውለው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

ህብረተሰቡ የጸጥታ ኃይሎችን የደንብ ልብስ በመልበስ፣ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ እና ህግ አስከባሪ በመምሰል ወደ መኖሪያ ቤቱ የሚመጡ ግለሰቦች ሁኔታ አጠራጣሪ ሆኖ ሲያገኝ ለአካባቢው ፖሊስ በመጠቆም ወይም በ987 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል ለፖሊስ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም