የህዳሴ ግድብን የተመለከተ ትክክለኛ መረጃ በአረብኛና በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በስፋት መሰራጨት አለበት

61

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ያሉ ትክክለኛ መረጃዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማድረስ በአረብኛና በሌሎች ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

በዓረብኛ ቋንቋ የሚሰሩ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን የተዛባ መረጃ እያሰራጩ እንደሆነም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን የህዳሴ ግድብ ስላለው ጠቀሜታና የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

ተወያያዮቹ በተለይ ከኢዜኣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በአባይ ወንዝ ላይ ግብጻዊያን ከልጅነታቸው ጀምሮ የተዛባ አመለካከት ይዘው ነው የሚያድጉት።

በዚህ ጉዳይ ከግብጻዊያን አልፎ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓና አሜሪካ ጭምር የተሳሳተ ግንዛቤ የሚያሲዙ ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎች የማሰራጨት ስራ በግብጽ በኩል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ይህንን የተሳሳተ መረጃ የሚያርም ትክክለኛ መረጃ በዓረብኛም ሆነ በሌሎች ዓለም ዓቀፍ ቋንቋዎች መሰራጨት እንደሚገባው የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የምትገነባው ግድብ ለግብጽም ጭምር ጠቀሜታ እንዳለው የግብጽ የውሃ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች ቢያውቁትም ህዝቡ ግን ከዚህ በተቃራኒ ምንም ግንዛቤ እንደሌለው ተናግረዋል።

''ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና የአገሪቱ ምሁራን አባይ ለግብጻውያን ብቻ ከፈጣሪ የተቸረ ስጦታ አድርጎ መመልከት ይታያል'' ብለዋል።

ይህን የተሳሳተ አመለከካት ለማስተካከል በአረብኛ ቋንቋ ለግብጽ ህዝብና ለሌላው የአረብኛ ተናጋሪ አገሮች ለማስገንዘብ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

እጩ ዶክተር ኢብራሂም ሀሰን ግብጾች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ሀሰተኛ መረጃዎችን እንደሚያስተላልፉ አንስተው፤ እውነታውን ለማውጣትና ለአለም ለማሳወቅ እንደሚጽፉ ገልጸዋል።

ሆኖም የምጽፈው መረጃ የሚሰራጨው በመንግስት ተቋም ሳይሆን በግሌ በመሆኑ በመንግስት በኩልም በአረብኛ የምንጽፋቸው ጹሁፎች በስፋት ተደራሽ እንዲሆኑ መሰራት ይኖርበታል ብለዋል።

ሙሃመድ አልአር አሩሲ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ሚዲያ ተገቢውንና በቂ የሆነ መረጃ ማቅረብ ይኖርበታል፤ የግድቡን ጠቀሜታ የግብጽ ባለሙያዎችም ያውቁታል ነገር ግን በግብጽ በኩል  አሁንም ኢትዮጵያ እንድትፈርምላት የምትፈልገው  የውሃው ባለቤት እሷ ብቻ እንድትሆን ነው።

ሁሴን አህመድ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ የአገር ጉዳይ በመሆኑ ስለ ግድቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ለግብጻዊያንና  ለሌላው አለም ተደራሽ ለማድረግ በአረብኛ ቋንቋ እየጻፍን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም የዓረቡ ዓለምና ሌላው የዓለም ህዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የፍትሃዊ ተጠቃሚት ጉዳይን የተመለከተ ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው በአረብኛ ቋንቋና በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አሁንም ብዙ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

እነሱም በአረብኛ ቋንቋ በተቻለ መጠን በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የአባይንና የህዳሴ ግድብ እውነታን እያስተዋወቁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብም በየትኛውም የአመለካከት ልዩነት ውስጥ እንኳ ቢሆን ግድቡን በተመለከተ ልዩነት ሳይኖረው መደገፍና ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የግድቡን የውሃ ሙሊት መጀመር በጉጉት እንደሚጠብቁትም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም