በአማራና በአፋር ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ትስስር አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው

111

ደሴ፣ ሰኔ 19/2012  ( ኢዜአ) በአማራና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም የህዝቦች ትስስር አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ወሎ ዞን መስተዳድር ገለፀ ።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማረም የሚያስችል የአንድ ቀን የጋራ ውይይት በወሎ ዩንቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሃመድ እንደገለጹት የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ አብሮ የመኖር የጋራ እሴት ያላቸው ናቸው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግጦሽ፣ በስርቆትና ዝርፊያና በሌሎች ምክንያቶች አለመግባባቶች ሲፈጠሩ መቆየታቸውን አውስተዋል።

የሚፈጠሩ ቀላል አለመግባባቶችንም የአገራችን ሰላም የማይፈልጉ ጸረ ሰላም ሃይሎች በማባባስ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም የሚከሰቱ ችግሮች ተባብሰው የሁለቱ ክልሎች ህዝቦችን የኑሮ ሁኔታ ከማመሰቃቀላቸው አስቀድሞ ህዝቡ ለዘመናት ያዳበረውን መልካም ግንኙነት በመጠቀም በመፍታት ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

በመጣው ለውጥ በመመስረትም በአዋሳኝ አካባቢዎች የጋራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን በማካሄድ የጋራ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።  

እስካሁን በተካሄዱ ውይይቶች የመጡ ለውጦችን ገምግሞ አጠናክሮ ለማስቀጠልና የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ውይይት ዛሬ በደሴ ከተማ መጀመሩን ተናግረዋል።

በውይይቱም የአማራና የአፋር ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በአቶ ተመስገን ጥሩነህና አቶ አወል አርባ የሚመራ የዞን፣ የወረዳና የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።