የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የደን ምንጣሮ ስራ ተጀመረ

213

አሶሳ ሰኔ 19 / 2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ የሚተኛበት ስፍራ ደን ምንጣሮ ስራ ትናንት ተጀመረ፡፡ 

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኡንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በሽር አብዱራሂም እንደገለፁት ክልሉ በኢንተርፕራይዞች አማካኝነት የሚመነጠር 1 ሺህ ሔክታር መሬት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ተረክቦ ትናንት የምንጣሮ ስራው እንዲጀመር አድርጓል ።

ግድቡ በመጪው ሐምሌ ውሃ ለመሙላት የተያዘውን እቅድ እንዲሳካ ከወዲሁ የደን ምንጣሮ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ 2ሺህ አባላት የያዙ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራው ገብተዋል ።

ኤጀንሲው የምንጣሮ ስራውን በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወን የቅርብ ክትትል ያደርጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ  የጤና፣ የጸጥታ እና ሌሎችም ቡድኖች ምንጣሮውን ከሚያካሂዱ ኢንተርፕራይዞች ጋር አብረው ወደ ስፍራው ገብተዋል ብለዋል፡፡

ለስራው የሚያስፈልግ በጀት እና ሌሎች ግብአቶች ለኢንተርፕራይዞቹ መቅረቡን አቶ በሽር ተናግረዋል ።

አጠቃላይ ለምንጣሮ ስራው 32 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለትም ከዋና ዳሬክተሩ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በደን ምንጣሮ ስራው መሳተፍ የጀመሩ ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ  አጠናቅቀው ለማስረከብ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በምንጣሮ ስራው ከተሳተፉት መካከል አቶ አለማየሁ መልካሙ እንዳሉት ምንጣሮው በተጀመረበት በትናንትናው ዕለት ብቻ ሁለት ሄክታር ያህል ደን የመመንጠር ስራ አከናውነዋል ።

ስራውን በሃገር ፍቅር ስሜት የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት በማሰብ ነው የምናከናውው ያለው ደግሞ ወጣት ሃሰን መንሱር ነው፡፡

የምንጣሮ ስራውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን እናስረክባለን ብሏል ፡፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን ያለማንም ፈቃድ የመጠቀም መብት አላት የሚለው ደሞ በደን ምንጣሮ ስራው የተሳተፈው ሌላው ወጣት ኢሳ ኢሳቅ ነው፡፡

የህዳሴው ግድብን ለማደናቀፍ በተለይ በግብጽ በኩል የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ መቆም አለበት ያለው ወጣቱ እነሱንም ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ ሊያግዙን ይገባ ነበር ብሏል ።

አሁን በተሰማራበት የደን ምንጣሮ ስራ ዜግነታዊ ግዴታውን በብቃት ለመወጣት መዘጋጀቱን ገልፆ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለግድቡ መጠናቀቅ የህይወት መስዋእትነት ጭምር ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል ።

በደን ምጣሮ ስራው መሳተፏ ደስተኛ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ሃናማርያም ንጉስ ነች፡፡

በሃገራችን በተመዘገቡ ያለፉ ታሪኮች ሁሉ የሴቶች ድርሻ የማይናቅ እንደነበር ወጣቷ ገልፃ ግድቡን ለማጠናቀቅ በተቃረብንበት ወቅት የምንጣሮ ስራው አካል መሆኗን እንደሚያስደስታት ተናግራለች ።

አባቶች ወራሪ ጠላትን አሳፍረው የመለሱበትን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ እኛ ልንደግመው ተዘጋጅተናል የምትለው ወጣቷ ለግድብ ፍጻሜ ርብርባችንን አጠናከረን እንቀጥላለን ብላለች ።