ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለጅቡቲ በዕርዳታ አቀረበች

257

ሰኔ 18 / 2012 ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና በሽታው ከተከሰተ በኋላም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ግምቱ ከ300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ዋጋ ያለው ልዩ ልዩ የህክምና መስጫ መድሀኒቶችንና ቁሳቁሶችን ለጅቡቲ በዕርዳታ አቅርባለች፡፡

እርዳታውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የጅቡቲ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በተገኙበት ዛሬ በጅቡቲ ኣምቡሊ ዓለም-አቀፍ ኤርፖርት በመገኘት አስረክበዋል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ሁለቱ አገራት ስትራቴጂያዊ አጋርና በመልካም ጊዜ ብቻ ሳይሆን እንደ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚከሰትባቸው አስከፊ ወቅቶችም በጋራ የሚቆሙ መሆናቸውንና የዛሬው ድጋፍም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አንስተዋል፡፡

ሁለቱ አገራት የጋራ ድንበር የሚጋሩ ከመሆናቸው አንጸር በሽታውን ለመከላከል በጋራ ተባብረው መስራት እንደሚገባቸውም የጠቀሱት ሚኒሰትር ዴኤታው በቀጣይም በጤናና ሌሎች ዘርፎች የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ከተከሰተም በኋላ ምላሽ ለመስጠት በአገር ውስጥ እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች በተጨማሪ ከጎረቤት አገራት ጋርም በመተባበር በድንበሮች አካባቢ ያሉትን የመድኃኒት አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከጅቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒሰትር መሀመድ የሱፍ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ አካባቢያዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁለቱ አገራት የጋራ ባህል፣ ቋንቋ እና ታሪካዊ ዳራ የሚጋሩና ስትራቴጂክ አጋር መሆናቸውን ጠቅሰው በሁሉም መስኮች ያሉትን የሁለቱን አገራት ግንኙነቶች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በማከልም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትር ሙሀመድ የሱፍ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዕርዳታ መልክ ላቀረበቻቸው የህክምና ግብዓቶች በጅቡቲ መንግስትና ህዝብ ስም የላቀ ምስጋናቸውን በማቅረብ ይህ ዓይነቱ ተግባር የሁለቱን አገራት ጥብቅ ወዳጅነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ጅበቲ እንደቀድሞ ሁሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንደምታከብርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም ከጎኗ እንደምትቆም አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይም ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስኮች ያሉትን ትብብሮች ይበልጥ ለማጠናከር ብሎም በቀጠናው ውስጥ ሰላምና ጸጥታን ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀራርቦ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡