የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን ተፈፃሚ የሚያደርግ ኮሚቴ ስራ ጀመረ

71
አዲስ አበባ ሀምሌ  2/2010 የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን ተፈፃሚ የሚያደርግ የጋራ ኮሚቴ ዛሬ ስራ ጀመረ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ኤርትራን በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በዲፕሎማሲ፣ በትራንስፖርት፣ በድንበር ጉዳዮች፣ በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድ እንዲሁም በአፍሪካና ዓለምአቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ስምምነት ፈርመዋል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጉብኝትና በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ዙሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች አስመራ ላይ ባደረጉት ውይይት የተደረሱትን ስምምነቶች ተግባራዊ የሚያደርግ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመዋል። ኮሚቴው በሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራ ሲሆን በውስጡም ሌሎች ንዑስ ኮሚቴዎች እንዳሉት ተናግረዋል። ኮሚቴው በዛሬው ዕለት ስራውን በይፋ መጀመሩና በስምምነቱ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን በጥልቀት ተመልክቶ የተለያዩ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብ ገልፀዋል። በስምምነቱ መሰረትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪው ሳምንት ወደ አስመራ በረራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል። ሁለቱም አገራት ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈት ከወዲሁ የቦታ ልየታ ስራ መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም