ለህዳሴ ግድብ አፍሪካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ኬንያ ገለፀች

69

ሰኔ 18/2012(ኢዜአ) ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለው ልዩነት ከፍጥጫ ይልቅ በድርድር ሊፈታ እንደሚገባው ኬንያ ገለፀች።

ኬንያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙረያ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል የሚካሄደው የሰስትዮሽ ድርድር “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” መርህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚገባ አስታውቃለች።

የኬንያ የውሃ፣ የሳኒቴሽን እና መስኖ ልማት ሚኒስትር ሲሲሊ ካሪዩኪ ዛሬ በኬንያ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለምን በጽ/ቤታቸው ባነጋገሩበት ወቅት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ መፈለግ የሚለው የኬንያ አቋም የፀና መሆኑን ተናግረዋል።

ከህዳሴ ግድብ ጋር ያለው ሁኔታ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ሊሆን እንደሚገባም ሚኒስትሯ ግልፀዋል።

አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው በኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን መካከል እየተካሄደ ስላለው የሶስትዮሽ ድርድር ገለፃ አድርገውላቸዋል። ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያለው የአቋም ልዩነትም ሁሉንም እኩል እና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሁም አሸናፊ በሚያደርግ የመተባበር መርህ ሊካሄድ እንደሚገባው ኢትዮጵያ ጽኑ አቋም እንዳላትም አምባሳደሩ አስረድተዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወጪ ወገንን ከድህነት ለማውጣት የሚሰሩት መሆኑን ጠቅሰው ፕሮጀክቱ ከራሳቸው አልፎ የቀጠናው ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እውን ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኬንያው ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ያሉ ልዩነቶች “አፍሪካዊ መፍትሄዎች ለአፍሪካ ችግሮች” መርህ እንዲፈቱ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

(በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ማህራዊ ገጽ)

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም