የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሠራተኞች ደም ለገሡ

98

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ሠራተኞች በዛሬው ዕለት ደማቸውን ለገሡ።

በኢትዮጵያ ኮቪድ -19 ከተከሰተ ወዲህ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቁጥር ቀንሶብኛል በማለት ብሔራዊ  የደም ባንክ አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል።

የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ "ደም ለግሡ" በማለት ጤና ሚኒስቴርም ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።

ይህንንም ጥሪ በመቀበልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎችና ማኅበረሰቡ የደም ልገሳ አድርገዋል።

በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሠራተኞች ደማቸውን ለግሰዋል።

ደማቸውን ሲለግሱ ከነበሩት መካከል የኢዜአ ዋና ሥራአስፈፃሚ አቶ ሠይፈ ደርቤ እንዳሉት ደም መለገስ ከምንም በላይ የኅሊና እርካታ ያለው ልዩ ሥጦታ ነው።

በመሆኑም "ነገ የምንቀበለውን ደም ዛሬ ላይ ደም ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መለገስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስን እየተከላከልን ባለንብት በአሁኑ ወቅት የደም ልገሳ ማድረግም የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በመሆኑም ኮሮናን እየተጠነቀቅን በደም እጦት ሕይወታቸውን ሊያጡ የሚችሉ ዜጎችን ሕይወት እንታደግ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢዜአ የባሕር ማዶ ሚዲያ ሞኒተሪንግና ትንተና ቡድን መሪ አቶ ገዛኸኝ ደገፉ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች ለማኅበረሰቡ መረጃ ከማድረስ በተጨማሪ ጥሩ አርዓያ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ለዚህም የተቋሙ ሠራተኞች ደማቸውን በመለገስ በጎነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

የኢዜአ የሴቶችና ባለ ብዙ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ እንዳሉትም ደም መስጠት ላይ የተሻለ ተነሳሽነት ቢኖርም አሁንም ብዙ ይቀራል ብለዋል።

በደም ልገሳ ዙሪያ በማኅበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት እንዳለ ገልጸው ደም ስንለግስ የሰዎችን ሕይወት እያተረፍን መሆኑን ስንረዳ የኅሊና እርካታ ይኖረዋል ብለዋል።

ለዚህም የኢዜአ ሠራተኞች ደማቸውን በመለገስ ለበጎነት አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

የብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ሙላት በቀለ በበኩላቸው የኢዜአ ሠራተኞች ያደረጉትን በጎ ተግባር በማድነቅ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

"ደም መለገስ የሰዎችን ሕይወት መታደግ የራስንም ጤና መጠበቅ ነው" ለዚህ በጎ ተግባር ሁሉም እንዲነሳሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሠራተኞች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደም በመለገስ እየተሳተፉ ሲሆን ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ ለግሠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም