ለብልጽግና ጉዟችን ስኬት ወደ ፊት ማየት ይገባል--- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ - ኢዜአ አማርኛ
ለብልጽግና ጉዟችን ስኬት ወደ ፊት ማየት ይገባል--- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ግቡን እንዲመታ ወደ ፊት ማየት ይገባል አሉ።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት ተካሂዷል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ በቀን በሦስት ዙር ሁለት ሚሊዮን ዳቦ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን ለ3 ሺህ 400 ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
ፋብሪካው የማኅበረሰቡን የዳቦ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የራሱን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ታምኖበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፋብሪካው ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁ ቁርጠኝነት ካለ ምንም ነገር ማደረግ እንደሚቻል አሳይቷል።
''ፋብሪካው የዳቦ ማምረቻ ብቻ አይደለም ያሉት'' ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷ በቀጣይ ለማከናወን የያዘችው ብልፅግና ጉዞ ስኬት አመላካች እንደሆነም ጠቁመዋል።
በቀጣይ ሌሎች ክልሎች ላይም አነስተኛ የዳቦ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የስንዴ ምርትን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ለመተካት ግብ መጣሉን ጠቅሰው የአገር ውስጥ ምርትን መቀበል የሚችሉ ፋብሪካዎች ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ለማሸጋገር የተያዘው ውጥን እንዲሳካም ወደፊት ማየት ያስፈልጋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከፋብሪካው ምርቃት በመቀጠል ከጎበኙ በኋላ በሥፍራው ችግኝ ተክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በበኩላቸው የዜጎችን ችግር ለማቃለል የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
''በዚህም የዳቦ፣ የታክሲና ሌሎች ሰልፎች እንዲቀሩ ተወጥኗል'' ያሉት ከንቲባው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ወደ ምርት መግባት የእዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አብራርተዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዜጎች ሕይወት እንዲቀየር የሚሰጡት አመራር ቁልፍ የችግር መፍቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሜድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብነት ገብረመስቀል እንደተናገሩት፤ ፋብሪካውን በሰድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክያት ሊዘገይ ችሏል።
የዳቦ ምርቱን ለመጀመር የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ግዥ ለመፈጸም ወረርሽኙ ጫና መፍጠሩን ጠቅሰው ከውጭ አገር ባለሙያዎች ማስመጣትም ሌላው ችግር እንደነበር አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግንባታው ቦታ ከመስጠት ባለፈ ለሰጠው ቁርጠኛ አመራርም አድንቀዋል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ከ41 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን የዱቄት ፋብሪካ፣ የሻይ ቅጠል ማቀነባበሪያዎችን የያዘ ነው።
ፋብሪካው 120 ሺህ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው አራት ጎተራዎችም አሉት።