በኢትዮጵያ ለሶስት አመታት የሚቆይ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና የጤና አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለሶስት አመታት የሚቆይ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና የጤና አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት የህፃናት አድን ድርጅት( ዩኒሴፍና ) የአለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለሶስት አመታት የሚቆይ የህፃናትንና የእናቶችን ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረገ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና የጤና አገልግሎት ተግባራዊ ሊያደርጉ ነው።
በአይነቱ የመጀመሪያ ነው የተባለው ትብብር፤ በኢትዮጵያ ያለውን አጣዳፊና ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ተብሏል።
ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ችግሩን ለማስወገድ የተደረገው ጥረት አመርቂ ውጤት እንዳላስመዘገበ ተገልጿል።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ በኮቪድ-19 ወረርሸኝ፣ በበረሃ አንበጣ መስፋፋት፣ በአየር ንብረት ፀባይ ለውጥ በሚከሰት ድርቅና የጎርፍ አደጋ ምክንያት በመጨመሩ ትብብሩ አስፈልጓል።
በዚህ አመት በአገሪቱ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
ከነዚህ መካከል 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህፃናት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ናቸው።
ተቋማቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን በማመናቸው በተመረጡ ወረዳዎች የሚገኙ የችግሩ ተጋላጭ ህፃናትንና እናቶችን በመለየትና ትምህርት ቤቶችንና ማህበረሰቡን በማሳተፍ የመከላከል ተግባር ለማከናወን ተነስተዋል።
ይህ ተግባር አገሪቱ እኤአ በ2030 የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ያለባቸውን ህጻናት አሁን ካሉበት 10 በመቶ ወደ 3 በመቶ ለመቀነስ የያዘችውን ግብ ለማሳካት እንደሚያስችላት ተጠቅሷል።
ዩኒሴፍና የአለም የምግብ ፕሮግራም በጋራ በመሆን ጉዳቱ ጎልቶ የሚታይባቸውን 100 ወረዳዎች ከአፋር ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች በመለየት እገዛውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።
በዚህም አገልግሎቱን ከሚያገኙ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች መካከል 70 በመቶ የሚጠጉትን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን እውቀትና የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአት እንደሚያሳድገው ታምኖበታል።
በተጨማሪ በአፋርና በሶማሌ ክልል በሚገኙ 600 ትምህርት ቤቶች የጤና እና የተመጣጠነ ምግብ መረጃን ለመስጠትና በክልሎቹ የሚገኙ 200 ሺህ ተማሪዎችን ለመመገብ ያስችላል።
"በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ያለባቸው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የበረሃ አንበጣ መስፋፋትና የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ተከትሎ ስጋቱን ከፍ የሚያደርግ ምልክት ማሳየታቸው ያሳስበናል” በማለት የዩኒሴፍ ተወካይ የሆኑት አዴል ኮዶር ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር የምናከናውነው ፕሮግራም ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍና ድጋፉ የሚያስፈልጋቸውን ህፃናትና እናቶች የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት እገዛ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት በምግብ፣ በጤና እና በትምህርት ላይ ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን እናውቃለን ” ያሉት ደግሞ የአለም የምግብ ፕሮግራም ወኪልና የኢትዮጵያ ተጠሪ ስቲቨን ኦማሞ ናቸው።
"አሁን የጀመርነው ትብብር ጥረታችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው እናምናለን ፤ በተጨማሪ መንግስት በአገሪቱ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ሸግግር ለማምጣት የያዘውን ራዕይ ይደግፋል" ብለዋል።
በአገሪቱ የሚታየውን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለመቅረፍ የአመጋገብ ስርአትን ማዘመንና የምግብ ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ ምግቦችን ለህፃናትና ለእናቶች ማቅረብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ረሃብንና የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ችግርን ለማቃለል አገራዊ መፍትሄ እና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ወሳኝ እገዛ ያበረክታል ተብሏል።