በዓሳ ማስገር ለተሰማሩ ማህበራት ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ሶስት ተሸከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ

114

ሰቆጣ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ዓሳ ማስገር ስራ ላይ ለተሰማሩ ማህበራት ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገዙ ሶስት ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው ተሸከርካሪዎች ድጋፍ ተደረገ።

ተሸከርካሪዎቹ በሃይቁ ያለውን እምቅ የዓሳ ሃብት በማውጣት ለሌሎች ከተሞች በማጓጓዝ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው  ተመልክቷል።

በአስተዳደሩ  እንስሳት ሃብት ጽህፈት ቤት የዓሳ ሃብት ልማት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዝናቡ ፍቃዱ እንዳሉት ተሽከርካሪዎቹ የተገዙት በክልሉ መንግስት ዘላቂ ልማት ፕሮጀክት ነው።

በፕሮጀክቱ ከ11 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተገዙት ተሽከካሪዎችም በተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ አዋሳኝ በሆኑት የሰሃላ፣ ዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳዎች በዓሳ ማስገር ለተሰማሩ ማህበራት ዛሬ  ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

የተሽከርካሪዎቹ መምጣትም በተከዜ ሃይቅ ያለውን እምቅ የዓሳ ሃብት አውጥቶ ወደ ተለያዩ ከተሞች በማጓጓዝ በዘርፉ የተሰማሩ አካላትን ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል።

ሃይቁ በሚያዋስናቸው ሶስት ወረዳዎች ከሶስት ሺህ 500 በላይ አባላትን ያቀፉ 15 የዓሳ አስጋሪ ማህበራት መደራጀታቸውን ጠቁመው በቀጣይ የጋራ ዩንየን በመመስረት አገልግሎት እንዲሰጡና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዝቋላ ወረዳ በዓሳ ማስገር ስራ ከተሰማሩት መካከል አቶ አምባየ አመረ  በሰጡት አስተያየት  ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከዜ ሃይቅ ላይ በዓሳ በማስገር ቢቆዩም በአካባቢያቸው የመሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አውስተዋል።

በዚህም የሚያመርቱት ዓሳ  የዘጠኝ ሰዓት የጀልባ ጉዞ በማድረግ ነጋዴው በሚወሰነው ዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ እንደነበር ጠቅሰው በዚህም ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ተናግረዋል።

አሁን የክልሉ መንግስት ማቀዝቀዣ ያላቸው የአሳ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎችን ድጋፍ ማድረጉ ያመረቱትን ዓሳ ወደ መሃል አገር በቀጥታ በመውሰድ ተወዳዳሪ በሆነ የገበያ ዋጋ ሸጠው ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።

በሃይቁ ያመረቱትን ዓሳ ወደ ገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸው ትራንስፖርት ባለመኖሩ ለምርት ብክነት እና ኪሳራ ሲጋለጡ መቆየታቸውን  የተናገረው ደግሞ የሰሃላ ወረዳ ነዋሪ   ወጣት ሃብቱ ዘገየ ነው።

"አሁን ላይ የክልሉ መንግስት የዓሳ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች ድጋፍ ማድረጉ በዘርፉ የተሰማራን ግለሰቦች የኑሮ ደረጃ እንዲለወጥ የሚያስችል ነው" ብለዋል።

በተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ በየዓመቱ  የሚመረተውን  ከሶስት ሺህ ቶን በላይ ዓሳ  ወደ ባህርዳር፣ ጎንደርና አዲስ አበባ በማጓጓዝ ሽጠው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውም የአስተዳደሩ እንስሳት ሃብት ጽህፈት ቤት  አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም