የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰራተኞች ችግኝ ተከሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰራተኞች በኢትዮጵያ ፋይናንስ ጥናት ተቋም ውስጥ ችግኝ ተከሉ። 

በአገር አቀፍ ደረጃ በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በመሳተፍ የተለያዩ ተቋማት ችግኝ እየተከሉ ይገኛሉ።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰራተኞች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኘው በኢትዮጵያ የፋይናንስ  ጥናት ተቋም ውስጥ 1 ሺህ 700 ችግኝ ተክለዋል።

ተቋሙ በዚህ ዓመት 5 ሺህ ችግኝ እንደሚተክል የባንኩ የሰው ሀብት አመራር ከፍተኛ ባለሞያ የሆኑት አቶ ጌታቸው ጀቢር ተናግረዋል።

ሰራተኞቹ የችግኝ ተከላውን ያከናወኑት በአረንጓዴ አሻራ ላይ በመሳተፍ በአገሪቷ የደን ልማት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መሆኑን ገልጸዋል።

ባንኩ ከሚሰጠው የፋይናንስ አገልግሎት በተጨማረ በአረንጓዴ ልማት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ባለፈው ዓመት 4 ሺህ ችግኝ በመትከል 98 በመቶ ያህል ማጽደቅ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመቀነስም የችግኝ ተከላው በተለያየ ዙር እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ ባለሙያ በመቅጠር የእንክብካቤ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ችግኞቹን በባለቤትነት በመንከባከብና ኮሚቴ በማቋቋም በተለየ ሁኔታ እንክብካቤ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ለማኖር በየዓመቱ የዛፍ ችግኝ መትከል ዘመቻ እየተተገበረ ሲሆን በዘንድሮ ክረምት 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ከግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም