ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሌሎችን ሕይወት እየታደጉ ያሉ የመንግስት ሠራተኞች ክብር ይገባቸዋል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

58

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2012 ( ኢዜአ) ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሌሎችን ሕይወት በመታደግ ላይ ለሚገኙ የመንግስት ሠራተኞች ክብር ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

18ኛው ዓለም አቀፍ የሲቪል ሰርቪስ ቀን በኢትዮጵያም ለ14ኛ ጊዜ ተከብሯል።

ቀኑ የተከበረው "ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ላሉ የሕዝብ አገልጋይ ሲቪል ሰርቫንቶች ክብርና ዕውቅና እንስጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የመንግስታቱ ድርጅትና የኮሪያ መንግስትም ቀኑን አስመልክተው የቪዲዮ ኮንፈረንስ አዘጋጅተዋል።

በኮንፈረንሱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖምና ሌሎችም ንግግር አድርገዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ የመንግስት አገልግሎቶች ላይም ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።

ይሁንና የመንግስት ሠራተኞች በወረርሽኙ መከላከልና መቆጣጠር ላይ እየተጫወቱት ያለው ሚና በቃላት ሊገለጽ የማይችል መሆኑን ነው ያነሱት።

በተለይም በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞች ሕይወታቸውን ጭምር መስዋዕት አድርገው ዜጎችን እያገለገሉ መሆኑን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ የሌሎችን ሕይወት ለሚታደጉ የጤና ባለሙያዎች በሲቪል ሰርቪስ ቀን ዕውቅናና ክብር መስጠት ተገቢና ወቅታዊ መሆኑንም አክለዋል።

በመንግስት ተቋም ተቀጥሮ የሚሰራ ሠራተኛ ድርብ ኃላፊነት ያለበትና በሌሎች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችል እንደሆነም ነው ፕሬዚዳንቷ የገለጹት።

ሲቪል ሰርቫንቱ በቅንነትና በታማኝነት የማገልገል ኃላፊነቱን በአግባቡ በመወጣት እያስመሰከረ ለመሆኑ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመንግስት ሠራተኞች በተቋም ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዚዳንቷ የኮሮና ወረርሽኝ ጠንካራ የጤና ስርዓትና ተቋም መገንባት ወሳኝ መሆኑን ያስተማረ ነው ብለዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ባስተላለፉት መልዕክትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ግንባር ቀደም በመሆን ሕዝብ እያገለገሉ ላሉ የመንግስት ሠራተኞች ክብር መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

የሕክምና ባለሙያዎች ሕይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ ሕይወት እየታደጉ መሆኑንና የጽዳት አገልግሎት ሠራተኞችም ምቹና ንጹህ የስራ ከባቢ በመፍጠር ጉልህ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉ ተዋንያንም የቢዝነስ እንቅስቃሴው ላይ የጎላ ጉዳት እንዳይደርስ እያበረከቱት ላለው ድርሻ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት።

ልጆችን በኦንላይን በመታገዝ በማስተማር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ላሉ መምህራንም ምስጋና አቅርበዋል።

የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ የስታትስቲክስና የመረጃ ባለሙያዎችም የኮሮና ስርጭትን አስመልክቶ ጠቃሚና ወቅታዊ መረጃዎችን በማሰራጨት ሕዝብን እያገለገሉ ይገኛሉ ብለዋል።

ሲቪል ሰርቫንቶች በአደገኛ የስራ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም የአገልጋይነት ሚናቸውን በአግባቡ እየተወጡ በመሆኑ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም