የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ድርድር አዎንታዊ ውጤት እንዲያመጣ ከአፍሪካ ኅብረት ጎን እቆማለሁ-- ጥቁር አሜሪካዊያን የኮንግረስ አባላት

85

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) የጥቁር አሜሪካዊያን የኮንግረስ አባላት ስብስብ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሶስትዮሽ ድርድር ሂደት አዎንታዊ ውጤት እንዲያመጣ ከአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ተዋናዮች ጎን እንደሚቆም ገለጸ። 

አሜሪካና ሌሎች ዓለምዓቀፍ ተዋናዮች በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል ያለውን የሶስትዮሽ የስምምነት መርህ እንዲያከብሩም ጠይቋል።

ስብስቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።

ሶስቱ አገራት የሕዳሴውን ግድብ በተመለከተ የሚያደርጉት ድርድር በትብብር መንፈስ መቀጠል ያለበትና በሁሉም ወገን በኩል ሠላማዊ የድርድር ሂደትን በመከተል መሆን እንዳለበት በመግለጫው አመልክቷል።

የድርድሩ መሰረት መቆም ያለበትም በጋራ ተጠቃሚነት፣ በመተማመንና የዓለም ዓቀፍ ሕግ መርሆችን በመከተል ሊሆን እንደሚገባም መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።

የሕዳሴው ግድብ መገንባት በቀጣናው ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት እምነቱን የገለጸው ጥቁር አሜሪካዊያን የኮንግረስ አባላት ስብስብ፤ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታቀርብ እንደሚያስችላትም ገልጿል።

አሜሪካና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተዋናዮች ሶስቱ አገራት እ.አ.አ በ2015 ያወጡትን የሶስትዮሽ የስምምነት መርህ እንዲያከብሩ የጠየቀው መግለጫው ''የድርድር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የሌሎች አካላት ሚና ካስፈለገ እንኳን የአፍሪካ ኅብረት ምክር ቤትና መቀመጫቸው በቀጣናው የሆነ ዲፕሎማቶች ይበቃሉ'' ብሏል።

በተለይም ደግሞ ሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች የሚያደርጉት ሠላማዊ ድርድርና ውጤት ጥቅሙ ለተወሰኑ አካላት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እንደሆነ ማስገንዘብ እንደሚጠበቅበት አመልክቷል።

የግድቡ ግንባታ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ባለው የውሃ ፍሰት፣ በኃይል አቅርቦትና የምግብ ዋስትና ሁኔታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሚኖረው አመልክቶ፤ ባለፉት ዓመታት በቀጣናው የድርቅ ክስተት መስተዋሉን አስታውሷል።

የግድቡ ግንባታ የሕዝብ ቁጥሯ እየጨመረ ለመጣው ግብጽ የተሻለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው በማመልከት፤ ''ግድቡ የግብጽን የውሃ አቅርቦት የሚያሻሽል ነው'' ብሏል።

የሕዳሴ ግድብ መገንባት በሱዳን ደግሞ የአገሪቱን የውሃ ቁጥጥር ለማሳለጥ፣ የደለል ጫናን ለመቀነስ የግብርና ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል ምርትን ለማሳደግና የጎርፍ ቁጥጥር ለማድረግ ወሳኝነት እንዳለውም አብራርቷል።

በአጠቃላይ የግድቡ መገንባት በሶስቱም አገራት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የጠቀሰው መግለጫው፤ የምግብ ዋስትናን ችግር ለመፍታት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የውሃ ፍላጎትን ለማርካትና የቀጣናውን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ሁለገብ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድቷል።

በመሆኑም የጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላት ስብስብ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የሚደረገውን ሠላማዊ የድርድር ሂደት እንደሚደግፍና የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ተዋናዮች ለሠላማዊ ድርድሩ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ በመደገፍ ለሁሉም ወገን የጋራ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም