በሰሜን ሸዋ ዞን የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ

58

ፍቼ፣ ሰኔ 16/2ዐ12 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ተዘጋጁ፡፡

ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት በመንግስትና  ህዝብ ድጋፍ በዞኑ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ ነው።

በምረቃው ስነስርዓት የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ብርሃኑ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ  ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት በመልካም አስተዳደር ሌሎች ችግሮች ምክንያት ሲጓተቱ  የቆዩ ናቸው።

የተገነቡት ፕሮጀክቶች  በቁጥር 253 እንደሆኑና ከመካከላቸውም  የጤና፣ ትምህርት፣ ግብርናና የገጠር መንገድ ፣ የወጣቶችን የስራ አጥነትና የመዝናኛ ችግር ለማቃለል የሚያግዙ የመስሪያና መሸጫ እንዲሁም የመዝናኛና ማሰልጠኛ ማዕከላት እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።

የአርሶ አደሩን ገቢና ኑሮ ለማሻሻል የሚረዱ የሰርቶ ማሳያ፣ የችግኝ ማፍያ፣ የመስኖ ግድብ፣ የእንስሳት መኖና ጤና ልማት ስራዎች ለአገልግሎት የተዘጋጁ ሌሎቹ የልማት ፕሮጀክቶች ናቸው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች  የተገነቡት በአብዛኛው የዞኑን ማህበረሰብ የልማት ፍላጐት መሰረት ያደረጉ  ናቸው ብለዋል፡፡

በምረቃው ስነስርዓት የተገኙት በኦሮሚያ ክልል ምክትል ኘሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው በክልሉ በበጀት ዓመቱ ከተለዩ ኘሮጀክቶች መካከል ሶስት ሺህ ዘጠኝ መቶ  በመጠናቀቃቸው በተያዘው ሳምንት ለአገልግሎት እንደሚበቁ አስታውቀዋል።

 ሌሎች የሕዝብ ጥያቄና ፍላጐት የሆኑ የልማት ስራዎችን በቅደም ተከተል  እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።

መንግስት የተቋረጡ የልማት ኘሮጀክቶች ግንባታቸውን በማስቀጠል ለማስፈጸም ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

አቶ አዲሱ በሕዝብ አቅምና ጥረት የሚከናወኑ ስራዎችን ጉልበት፣ ቁሳቁስና ገንዘብን አስተባብሮ መስራት በየአካባቢው ሊለመድ እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ማህበረሰብ የቆየውን የጀግንነትና የስራ ባህል ዛሬም በልማቱ መስክ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአካባቢው የሀገር ሽማግሌ አቶ ማሞ በላቸው በሰጡት አስተያየት ለአገልግሎት የተዘጋጁት ተቋማት  ለማህበረሰቡ ልማትና  እድገት  እንደሚበጁ ገልጸው ነዋሪዎችም አካባቢያቸውን አረንጓዴ ለማልበስ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የውጫሌ ወረዳ ነዋሪ ሀደ ስንቄ ፈዩፍቱ ሞቲ በበኩላቸው በአካባቢያቸው የተሰራው ሆስፒታል የነበረባቸውን ጤና አገልግሎት ችግር ለመፍታት መሰረት ያደረጉ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የግራር ጃርሶ ወረዳ ነዋሪ መምህር መርሻ ውድነህ እንዳሉት  አዲሱ የመንግስት ለውጥ ኃይል ተረስተው የነበሩ የከተማና ገጠር የልማት ስራዎችን በማንቀሳቀስ ለውጤት ማብቃቱ የሚደገፍ ነው።

ተመሳሳይ መጓተትና መዘግየት እንዳይኖር  መንግስት ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ ችግሮችን ለማስወገድ መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም