ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ላይ ግብፅ በምታሳየው ወላዋይ አቋም ማዘኗን አስታወቀች

76

ሰኔ 16/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን እውነተኛ አቋም በድጋሜ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሳወቋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ ያላትን የማያወላውል አቋም ለሁለተኛ ጊዜ ለድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት በደብዳቤ አሳውቃለች።

ይህም ደብዳቤ ግብፅ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ መሆኑን በሚኒስቴሩ የዲጅታል ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር ጀነራልና ምክትል ቃል አቀባይ አቶ አምሳሉ ትዛዙ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ ላይ ግድቡ የሰላም እና ፀጥታ ስጋት አለመሆኑንም አስታውቃለች።

ግብፅ በሦስቱ አገራት መካከል እየተካሄደ ያለውን ድርድር በመተው ለምክር ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ ያስገባችው ደብዳቤ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም ም/ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፤ ግብፅ ለፀጥታው ምክር ቤት ያቀረበችው ጥያቄም አግባብ እንዳልሆነና በዚህ ድርጊት ማዘኗን በላከችው ደብዳቤ ማሳወቋን አቶ አምሳሉ አክለው ተናግረዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለፀጥታው ምክር ቤት የተላከው ደብዳቤ፤ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታችኛውን ተፋሰስ አገር እንደማይጎዳ እና የሰላም እና ፀጥታ ስጋትም አለመሆኑን በድጋሜ ማረጋገጥ መቻሉን ተመልክቷል።

የግብጽ አካሄድ ኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ የፖለቲካና እና የዲፕሎማሲ ጫና ለማሳረፍ መሞከር እንደሆነም በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህም ሌላ በቅኝ ግዛት ወቅት የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን ሳያሳትፍ የተደረገን ስምምነት እንደመደራደሪያ ሀሳብ ማቅረብም አግባብ እንዳልሆነም አቶ ገዱ በላኩት ደብዳቤ ላይ መገለጹን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ከዚያም ባለፈ አሁን እየተካሄደ ያለው ድርድር በውሀ ክፍፍል ሳይሆን በግድቡ የውሃ አሞላል ሂደት ላይ መሆኑንም በደብዳቤው ላይ ግልፅ መደረጉም ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ አሁንም በፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ የምታደርገውን ድርድር የመቀጠል ፍላጎት እንዳላት እና የትኛውንም የተፋሰሱ ሀገራት ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ግድቡን ለማጠናቀቅ ያላትን ቁርጠኝነት ለምክር ቤቱ አረጋግጣለች።

ኢትዮጵያ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት የሰላምና ፀጥታ ስጋት ካለም ሁልጊዜ የሀይል አማራጭን ለመጠቀም ስታስፈራራ የኖረችው ግብፅ ለዚያ ተጠያቂ እንደምትሆን ማሳወቋን አቶ አምሳሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም