ሊደርሱ የነበሩ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ ተችሏል-- ኢመደኤ

65

ሰኔ 16/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን  የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ሰኔ 10 12 13 እና 14/2012 . መቀመጫቸው ን ግብጽ ያደረጉ የሳይበር ወንጀለኞች በኢትዮጵያ የኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ለመፍጠር የተቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፉን አስታውቋል።

የሳይበር ጥቃት ሙከራው የተቃጣው ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ (Cyber_Horus Group) አኑቢስ ዶት ሃከር (AnuBis.Hacker) እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ (Security_By_Passed) በተባሉ የሳይበር አጥቂዎች አማካይነት መሆኑን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡

ወንጀለኞቹ ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጁ የቆዩ እና ኤጀንሲው ሲከታተላችው የነበሩ ሲሆን በይበልጥ አርብ ሰኔ 12/2012 እና ቅዳሜ ሰኔ 13/2012 ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውን ገልጿል።

በዚህ ጊዜ ዉስጥ 13 የመንግስት፣ 4 መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ድረ-ገጽን የማስተጓጎል ሙከራ ማድረጋቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል፡፡

የሳይበር ጥቃት ሙከራው በሀገሪቱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፤ የደህንነት መስሪያ ቤቶች እና የግል ድርጅቶች ድረ-ገጽ ላይ ያነጣጠረ ነበር ተብሏል፡፡

ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ፣ አኑቢስ ዶት ሃከር እና ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ የሳይበር ጥቃት አድራሽ ቡድኖች ሃላፊነቱን የወሰዱ ሲሆን ዋና አላማቸውም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በተለይ ከውሃ አሞላል ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ተጽእኖ በሀገሪቱ ላይ ለመፍጠር በማሰብ እንደፈጸሙት ተገልጿል፡፡

የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው ተቋማት አብዛኛዎቹ በድረ-ገጽ ግንባታ ሂደት ደህንነታችው ታሳቢ ያላደረጉ ተቋማት፤ በቀጣይነት የደህንነት ፍተሻ ያላደረጉ እና ከፍተኛ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት የነበረባቸው መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አረጋግጧል፡፡

ኤጀንሲው አስቀድሞ ቅድመ ዝግጅት በማድረጉ ምክንያት እና ይህን መጠነ ሰፊ የሳይበር ጥቃት መከላከል ባይችል ኖሮ ጥቃቱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፤ ፖሊቲካዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችል እን ደነበር የገለጸው ኤጀንሲው፤ በመከላከሉም ሊደርሱ የሚችሉ ከፍተኛ አደጋዎችን ማስወገድ መቻሉን እና ይህንንም ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት አሳውቋል፡፡

በቀጣይም መሰል ጥቃቶች በስፋት፤ በረቀቀ መንገድ እና ከተለያዩ ስፍራ ሊሰነዘር እንደሚችል ግምት ውስጥ በማስገባት ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት .et domain ከመጠቀማቸው በፊት የድረ-ገጻቸውን ደህንነት አረጋግጠው እንዲጠቀሙ፤ ራሳቸውን ከሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ለመከላከል እና አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚኖርባቸው ኤጀንሲው አሳስቧል።

ተቋማት ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ያለባቸውን የደህንነት ተጋላጭነት መድፈን እንዳለባችው እና የተለያዩ የሳይበር ደህንነት ጥቃት ሙከራ ሲያጋጥማቸውም ሆነ ሙያዊ ድጋፍ ሲያሻቸው ለኤጀንሲው በማሳወቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማግኘት እንደሚችሉ አስታወቋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት ትብብር ላደረጉልን ተቋማት እና ግለሰቦች በተለይ ለኢትዮ ቴሌኮም፣ ለኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ምስጋና ማቅረቡን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም