”አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም ! ”

130

 ”አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም! ” ገብረህይወት ካህሳይ /ኢዜአ/

”ዜግነት ለየትኛውም ሀገር ቢሆን ኩራት ነው። ሰዎች ስብእናቸው ሙሉ የሚሆነው መጠሪያ ሀገር ሲኖራቸው ነው። ይህ መጠሪያ ሀገር ኢትዮጵያዊ ሲሆን ደግሞ ትርጉሙ እጅግ በጣም ልዩ ነው”።

 ”እንደ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነትን ፣ አልገዛም ባይነትን ፣ ህብርን ፣ አሸናፊነትን ፣ በምዕራባዊያን ያልተበረዘ የሀገር ፍቅርን የሚያወድስ ሌላ ዜግነት ካለ እንወራረድ በሉኝ እወራረዳለሁ ”። አቶ ዮናስ ቬጋስ 

”በዚህ በኮሮና ዘመን ሌሎች ስራ ፈትተዋል። እንዲያውም ትዳራቸውን ጭምር ፈትተዋል። እኛ ግን ወንበር ፈትተን እየሰራን ነው”። ኮሜዲያን ፍልፍሉ 

”ኢትዮጵያን የምንወድ ከሆነ አገራዊ ምልክታችንን ልንጠብቅ ይገባል” አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ 

” ሰው ጠንክሮ ከሰራ ያሰበበት ደረጃ ላይ መድረስ እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው ” ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ 

” ዶሮ አንድ እንቁላል ለመጣል የተኛ ህፃንና በሽተኛን ጭምር ትቀሰቅሳለች። ጥሬ ካልቀረበልኝም ትላለች። ዓሳ ግን ያለ ድምፅ በአንድ ጊዜ በርካታ እንቁላሎች ትጥላለች።” አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ 

” ሀይቅ ዳር ያሉ እንቁራሪቶች ብዙ ይጮኃሉ። ሀይቁ የእነሱ ይመስላቸዋል። ሀይቁ ውስጥ ግን ዝም ያሉ ብዙ ትላልቅ ዓሳዎች ይኖራሉ። ” ረዳት ፕሮፌሰር ሶፊያ ከበደ 

”የኖህ ልጆች ኖህ አንድ ጊዜ የሆነ ስህተት ሰርቶ በፎረሸ ጊዜ ገበናውን ልጆቹ ሸፈኑለት። አንዱ ክፉ ልጅ ግን ገበናውን አጋለጠው። እናም ተረገመ ” አርቲስት አስቴር በዳኔ

”በናይጀሪያዊያን አባባል ”በእያንዳንዱ 12 ውስጥ አንድ ይሁዳ አይጠፋም ” አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም 

ሰሞኑን በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች ፣ ዝነኛ አርቲስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አንድ ቦታ ላይ ተገናኝተዋል። ከላይ የተቀነጨቡት አባባሎች በመድረኩ ላይ የተነሱ ናቸው። ንግግሮቹ የተለያዩ ቢመስሉም ይዘታቸው ግን አንድ ነው ።

ሁሉንም ወገኖች አንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው የመሰላቸውን እንዲናገሩ መድረኩን ያዘጋጁት ደግሞ አቶ ዮናስ ጂ. ዓለሙ ይባላሉ። ዮናስ ቬጋስ በሚል ቅፅል ስም ይታወቃሉ። አቶ ዮናስ ለ22 ዓመታት በአሜሪካን አገር የኖሩ ዲያስፖራ ናቸው። አሁን ወደ አገራቸው ተመልሰው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተዋል።

”እንደ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነትን ፣ አልገዛም ባይነትን ፣ ህብርን ፣ አሸናፊነትን ፣ በምእራባዊያን ያልተበረዘ የሀገር ፍቅርን የሚያወድስ ሌላ ዜግነት ካለ እንወራረድ በሉኝ እወራረዳለሁ”። የሚሉት አቶ ዮናስ መድረኩ እውነታውን አውቀን ችግሮች ካሉ በመፍትሔው ዙርያ የምንመክርበት ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

”የኢትዮጵያ ……….. ” ETHIOPIAN…….. ብሎ የሚጀምር መጠሪያ ”የእኛነትን” መንፈስ ያጭራል። እኛ ደግሞ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ነን። የኢትዮጵያ አየር መንገዱ የእኛው ንብረት መሆኑን ያመላክታል። 

ወገቡ ላይ የሚታየው አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን ደግሞ ከንብረትነቱ ባኛገር መገለጫ ዓርማችን መሆኑ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

አየር መንገዱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክፉም ሆነ በመልካም ጎኑ ተደጋግሞ ሲነሳ ይስተዋላል። ከላይ የተጠቀሱት ታዋቂ ግለሰቦች፣ ዝነኛ አርቲስቶችና የመገናኛ ብዙሃን የተሰባሰቡትም በቦታው ተገኝተው እውነታውን እንዲመለከቱ ለማድረግ ነበር ።

በቦታው የተገኙት የኢዜአ ሪፖርተሮች የጉብኝቱንና የውይይቱን ሙሉ ይዘት ተከታትለው በምስልና በድምፅ አስቀርተውታል።

አቶ ዮናስ እንደገለፁት የመሰባሰቡ ዓላማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስሙና ዓርማው ብቻ ሳይሆን ንብረትነቱም የሁላችን በመሆኑ የሚወራውና በተጨባጭ ያለውን እውነታ አስመልክተን በጋራ ለመመካከር ነው ብለዋል።

የተቋሙ ስኬት ስኬታችን ፣ ጉድለቱ ጉድለታችን ፣ ሽልማቱ ሽልማታችን ሀሜቱ ደግሞ ሀሜታችን ነውና እውነታውን ለማወቅ ያለውን ተመልክተን እውነታውን እንገንዘብ የሚል መልእክት አስተላለፉ።

አየር መንገዱ የሀገር መገለጫ፣ የኢኮኖሚ ዋልታና የኢትዮጵያዊያን የቀዳሚነት ማሳያ መሆኑን በመግለፅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድና የሽያጭ ስራ ክፍሎች ዋና ኃላፊና የአየር መንገዱ ምክትል ስራአስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም አጠቃላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጋበዙ።

 የኢትዮጵያ የሚል ስም ያስቀደመው አየር መንገዳችንን በመጥቀስ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ቀዳሚ መሆኗን ማብራራት ጀመሩ። ”ኢትዮጵያ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ከናይጀሪያ ቀጥሎ ብዙ ጥቁር ህዝቦች ያላት ሁለተኛዋ ሀገር ናት”።

” ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የዓለም ቃል ኪዳን ማህበር ሲመሰረት ኢትዮጵያ ብቸኛዋ አንዲት የጥቁር ህዝብ ድምፅ ነበረች ” የሚሉት አቶ ኢሳያስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላም የተባበሩት መንግስታት 

ድርጅት ሲመሰረት ቀዳሚ መስራች አገርና የጥቁሮች ድምፅ እንደነበረች አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋቋመው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1945 ነው። በ1946 የመጀመሪያ በረራው ወደ ካይሮ አደረገ። ያኔ ታዲያ ኢትዮጵያ የምትባል ነፃ ሀገር ነበረች። 

ሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ግን ነፃ የወጡት ከ1960ዎቹ ጀምሮ መሆኑን ይገልፃሉ። በወቅቱ ከምእራብ አፍሪካ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ለመሔድ በለንደንና በፓሪስ በኩል ዙርያ ጥምጥም ጉዞ ለማድረግ ግድ ነበር።

ታዲያ ! ኢትዮጵያና አየር መንገዷ ይህንን ችግር ለመፍታት Bring Africa Together የሚል ኮሜርሻል መፈክር በማንገብ የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡ አደረገ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት 127 አውሮፕላኖች አሉት። ይህን ደግሞ በአፍሪካ አንደኛ ያደርገዋል። በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘው ግብፅ ስትሆን 68 አውሮፕላኖች አሉዋት። እንደ አቶ ኢሳያስ አገላለፅ ኢትዮጵያና ግብፅ በአውሮፕላን ብዛት ሲነፃፀሩ ኢትዮጵያ አንደኛ ብቻ ሳትሆን ትልቅ አንደኛ ነች ማለት ይቻላል።

በአፍሪካ ከ60 በላይ መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ደግሞ አፍሪካን ከቀሪው ዓለም ለማገናኘት መዳረሻዎቹ ከ120 በላይ ከፍ አድርጎታል።

አየር መንገዳችን በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ካሉት አራት ምርጥ አየር መንገዶች አንዱ መሆኑንም አቶ ኢሳያስ ይናገራሉ። እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2004 የአምስት ዓመት እቅድ አዘጋጀ። ቀድሞ እቅዱን በማሳካቱ እንደገና ከ2010 እስከ 2025 የሚተገበር የ15 ዓመት ራእይ ይዞ መጣ። ይህም ከ8 ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙጥጥ አድርጎ አሳካው ይላሉ።

አሁን ላይ አየር መንገዱ የካርጎ ተርሚናሉን፣ አውሮፕላኖችን፣ ኤርፖርቶቹንና ሌሎችን ጨምሮ አሴቱ 10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። አጠቃላይ ዋጋው ደግሞ 350 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚደርስ ምክትል ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል።

አየር መንገዱ አምና 4 ቢሊዮን ዶላር ዘንድሮ ደግሞ 5 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝም አቶ ኢሳያስ ያስረዳሉ። ይህ ማለት ደግሞ በዓመት 175 ቢሊዮን ብር መሆኑ ነው። አገራችን ዘንድሮ ካፀደቀቸው አጠቃላይ በጀት ጋር አያይዘን ስንመለከተው 70 በመቶ አካባቢ የሚደርስ ነው።

ከአጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚ (GDP) አንፃር ቢታይ ደግሞ 5 በመቶ ይሸፍናል። 20 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓይነት ስኬታማ ተቋማት ቢኖሩን ድምራቸው የአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያክል ይሆናል ማለት ነው።

የአየር መንገዱ የስኬት ጉዞ ግን እንዲሁ አልጋ በአልጋ አልነበረም ይላሉ። ሳርስን ፣ የአሜሪካው የመስከረም 11 ፍንዳታን የመሳሰሉት በርካታ ፈተናዎች ተጋፍጧል።

ዘንድሮ ደግሞ ኮሮና ከባድ ፈተና እንደሆነበት ያስረዳሉ። ያም ሆኖ ግን ፈተናውን በፅናት ለመቋቋም እየሰራ ነው ብለዋል። ሌላው ፈተና አሁን በማህበራዊ ድረ ገፅና በአንዳንድ ሚዲያዎች እየታየ ያለው ሁኔታ ነው ይላሉ።

በአየር መንገዱ ላይ እየተካሔደ ያለው የማጠልሸት ዘመቻ ከእውነት የራቀ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪም የማይወደው ነው ይላሉ። ሞተር ተዘርፎ ተሸጠ ከሚለው ጀምሮ ወደ ቻይና እየተመላለሰ በኮሮና ሊያስጨርሰን ነው እስከሚለው ይደርሳል።

ታዲያ አየር መንገዱ ጉድለት ቢኖረው እንኳን የለውም እንጂ ገመናችንን ለውጭ ተወዳዳሪዎች አሳልፈን መስጠት አለብን ወይስ የቤታችን ጣጣ ተመካክሮ መፍታት ? ብለው ይጠይቃሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና የሚያደርገውን ጉዞ ቢያቋርጥ እንኳን ሌሎች አየር መንገዶች እስካላቋረጡ ድረስ ኮሮና በሌላ መንገድ መምጣቱ አይቀርም ባይ ናቸው። ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን ኮሮና የተገኘበት ሰው በዱባይ አየር መንገድ የመጣ ነው። 

ሁለተኛው ሰውም ቢሆን በአየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከቻይና ሳይሆን ከቡርኪናፋሶ ኡጓዱጉ ነው። ሁሉም መዳረሻዎች ይዘጉ ቢባል ደግሞ አገሪቷና ህዝቦቿ ምን ይሆናሉ? ባይ ናቸው። 

ወደብ አልባ አገር ይዘን አጣዳፊ ችግሮቻችን የምንፈታው በአየር ትራንስፖት መሆኑን ካለፈው ልምዳቸው በመነሳት ያስረዳሉ። የስኳር በሽታ መድሃኒት ሲያልቅ በፍጥነት አድርስልን የሚባለው አየር መንገዱ ነው።

ኮሮናን ተከትሎ አብዛኛዎቹ ትላልቅ አየር መንገዶች ሰራተኞቻቸውን ቀንሰዋል። የሰራተኞች ደመወዝም በግማሽ ለመቀነስ ተገደዋል።

ይህንኑ እንዳያደርጉ ደግሞ ከየራሳቸው መንግስታት ድጎማ ተደርጎላቸው እንኳን ገንዘቡ ከተቀበሉ በኋላ የሰራተኛ ደመወዝ የቀነሱ በርካቶች ናቸው ይላሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን የመንግስት ድጋፍ እንዳይጠይቅ አገራዊ አቅማችንን ያውቃል። የመንገደኞች ወንበርን እየፈታ ዕቃ በማመላለስ ሰራተኞች እንዳይቀነሱና ደመወዛቸው እንዳይሸራረፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል ።

17 ሺህ ሰራተኞች የያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአማካይ 5 ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ቢሆኑ እንኳን 85 ሺህ ሰዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በደመወዝ ያስተዳድራል ማለት ነው። 

ሆቴሎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ የቅርሳ ቅርስ ነጋዴዎች፣ የቱሪዝም ድርጅቶችና አስጎብኚዎች ጭምር ከዘርፉ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ያስረዳሉ።

አብዛኛው ሀገራችን ከምታስገኘው የውጭ ምንዛሪ ድምር ገቢ አየር መንገዱ ብቻውን የሚያስገኘው ገቢ ይበልጣል ሲሉም ምክትል ስራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

በአየር ላይ መንገደኞችን ሲያስተናግዱ የነበሩ የበረራ አስተናጋጆች በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ” የማእድ ማጋራት ” ጥሪ መሰረት በምድር ላይ የተቸገሩ ወገኖችን በማስተናገድ ላይ እንደሚገኙ ከአቶ ኢሳያስ ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

የናይጀሪያ፣ ታንዛኒያ፣ ጋናና ዛምቢያ አየር መንገዶች ከጨዋታ ውጭ በሆኑበትና የኬንያና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ደግሞ የውድቀት መንገድ በተያያዙበት ወቅት ፈተናዎች በፅናት እየተጋፈጠ በስኬት ጎዳና ላይ የሚገኘው የአየር መንገዳችን ላይ የተከፈተው የማጥላላት ዘመቻ ምን ይባላል ? ብለው ይጠይቃሉ።

ኮሮና ከአየር መንገዳችን ፣ አየር መንገዳችን ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ጋር በማያያዝ በውሸት ላይ የተመሰረተ ጥላሸት ለመቀባት መሞከር ሌላ ድብቅ አጀንዳ ከሌለው በስተቀር ውኃ የሚያነሳ ምክንያት እንደሌለው አስረድተዋል።

አሳማኝ ምክንያት ሳይኖር የተከፈተው የአሉባልታ ዘመቻ በጤናማው ገበያ ተወዳድረው ማሸነፍ ለተሳናቸው የአየር መንገዱ ተፎካካሪዎች ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ለእኛው ለኢትዮጵያዊያን ግን ከኪሳራ የዘለለ አይሆንም።

” ዓይን ዓይናችን ብላችሁ ካጠፋችሁን የራሳችሁ ዓይን አጠፋችሁ ” ማለት ነውና እባካችሁ ከድርጊታችሁ ታቀቡ ሲሉም የተማፅኖ መልእክት አስተላልፈዋል። 

በናይጀሪያዊያን አባባል ”በእያንዳንዱ 12 ውስጥ አንድ ይሁዳ አይጠፋም ” ሆኖም ግን ”አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም ” ሲሉም መኩሪያችን ፣ አለኝታችን ፣ መገለጫችን የሆነውን አንድ ለእናቱ አየር መንገዳችን በተሳሳተ መልኩ ልንጎዳው አይገባም ብለዋል።

የአየር መንገዱ ጓዳ ጎድጓዳ ተዘዋውረው የተመለከቱና ሰፊ ማብራሪያ የተሰጣቸው ታዋቂ ግለሰቦች ፣ አርቲስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ቆይታቸውን አስመልክተው በተለያየ አገላለፅ ግን ደግሞ አንድ ዓይነት ይዘት ያለው አስተያየት ሰጥተዋል። 

ቀድሞ ቁምነገር አዘል ቀልድ በማቅረብ ታዳሚዎችን ፈገግ ያስደረገው ኮሜዲያን ፍልፍሉ ነበር ” ። ሌሎች አየር መንገዶች ስራ ፈትተዋል። አየር መንገዳችን ግን ወንበሩን ብቻ በመፍታት የሰው ማጓጓዣው ዕቃ እንዲጭን አድርጎ እየሰራ ነው ” ሲል አድናቆቱን ገልጿል።

አርቲስት አስቴር በዳኔ የታዳሚዎችን ቀልብ የገዛ ንግግር አድርጋለች” አንዳንዴ በጣም እንደ አንድ ዓይን የምናያቸው ትልልቅ ነገሮች የማይሆን ነገር እንኳን ብናይ ዞር ማለት አለብን። ዝም ብለን ተረባርበን ዓይኑን ማጥፋት የለብንም ” ብላለች።

”የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የሚያሳዝን ሚስኪን ህዝብ ነው። የእኔ ነው ላለው ነገር ግን ይሞትለታል። የኢትዮጵያ ህዝብ እየራበው በግል ህይወቱ ላይ ስኬትን ማስመዝገብ ሲያጣ እንኳን እነ ኃይሌ ገብረስላሴ አሸንፈው ባንዲራ ሲይዙ ዋንጫው የእኔ ነው ብሎ ጠግቦ የሚያድር ህዝብ ነው ” ስትል አክላለች።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆነ አየር መንገድ ነው ያለችው አርቲስቷ ” ህዝቡ አእምሮው ውስጥ ከራሱ ኑሮ ፈልጎ አሪፍ ነገር እንኳን ቢያጣ ፤ በራሱ ኑሮ ሽልማት ሲያጣ ግድ የለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእኔ ነው። ኢትዮጵያዊነቴ ከፍ የሚያደርግልኝ ነው ” ብሎ እንደሚፅናና አብራርታለች።

” የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉሙ ላይ ነው የሚውለው አይደለ ? ከፍ ያለ ነው አይደለ ? ትንንሽ ነገር ማውራት አቁሙ። ሀሜተኛ ያውራ። መድረክ ከፍታችሁ ግን ለትንንሽ ነገር እጅ አትስጡ ” ስትልም ምክር ለግሳለች።

”የኖህ ልጆች ኖህ አንድ ጊዜ የሆነ ስህተት ሰርቶ በፎረሸ ጊዜ ገበናውን ሸፈኑለት። አንዱ ክፉ ልጅ ግን ገበናውን አጋለጠው እናም ተረገመ ” በማለት አሉባልታው የጥቂቶች መሆኑን ጠቁማለች።

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚመላለሱ አፍሪካዊያን የእኛ አየር መንገድ በጣም አሪፍ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ መስማቱን ገልፆ የእናንተ አየር መንገድ ምን ተብሎ ይጠራል ብሎ ሲጠይቃቸው ” የኢትዮጵያ አየር መንገድ ” ብለው እንደመለሱለት ያስታውሳል።

”የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሸነፈ ሲባል አገራችን አሸነፈች” ማለት ነው የሚለው ሻለቃ ኃይሌ ብቸኛ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ተቋማችን ነው ሲል ይገልፀዋል።

”ኢትዮጵያን የምንወድ ከሆነ አገራዊ ምልክታችንን ልንጠብቀው ይገባል” አየር መንገዳችንን እኮራበታለሁ ብሏል።

” ዶሮ አንድ እንቁላል ለመጣል የተኛ ህፃንና በሽተኛን ጭምር ትቀሰቅሳለች። ጥሬ ካልቀረበልኝም ትላለች። ዓሳ ግን ያለ ድምፅ በአንድ ጊዜ በርካታ እንቁላሎች ትጥላለች” ያለው ደግሞ ታዋቂው አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም በሩን በዘጋበት ወቅት ችግሮችን ተቋቁሞ ለመውጣት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልፇል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሶፊያ ከበደ በበኩላቸው ” ሀይቅ ዳር ያሉ እንቁራሪቶች ብዙ ይጮኃሉ። ሀይቁ የእነሱ ይመስላቸዋል ። ሀይቁ ውስጥ ግን ዝም ያሉ ብዙ ትላልቅ ዓሳዎች ይኖራሉ። ” ካሉ በኋላ የተንጫጫ ሁሉ እውነት አይደለምና ስራችሁ ላይ አተኩራችሁ ቀጥሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ የትራፊክ እንቅስቃሴ መረጃ በመስጠት የምናውቀው ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በበኩሉ በሀገራችን የኢትዮጵያ አየር መንገድና የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ሰራተኛ መሆን እንደኩራት ሲታይ መቆየቱን ያስታውሳል።

የአየር መንገዱ ስኬት ”ሰው ጠንክሮ ከሰራ ያሰበበት ደረጃ መድረስ እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው” ያለው ኢንስፔክተሩ የግለሰብ ፍላጎት የማህበረሰብ ፍላጎት አስመስለው ወሬ የሚያራግቡትን ተገቢነት የለውም ብሏል።

”የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓርማችን ፣ እናታችን ፣ ባንዲራችንና አገራችን ነው!። ስለዚህ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥቷል።

በቦታው የተገኙ ታዋቂ ግለሰቦች ፣ አርቲስቶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ያስማማ አንድ ነገር አለ። አየር መንገዱ በሩን ዘግቶ ለአሉባልታ ከሚጋለጥ ክፍት አድርጎ ዜጎች እውነታውን እንዲገነዘቡት ማድረግ አለበት የሚል ነው። 

ታዲያ ! ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆኑን ታሳቢ ተደርጎ በሩን ክፍት ያድርግ ሲባል ሚስጢርን ለተወዳዳሪዎቹ አሳልፎ በማይሰጥ መልኩ መሆን አለበት ተብሏል።

”አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም ” ይባል የለ? በአፈር ስንጫወት የራሳችንን ዓይን በራሳችን እጅ እንዳናጠፋ ጠንቀቅ ማለቱ ይበጃል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም