በድምጽ የሚታዘዝ የእጅ መታጠቢያ ማሽን ተሰርቶ ለአገልግሎት በቃ

1922

ቢሾፍቱ፣ ሰኔ 15/2012 (ኢዜአ) በድምጽ የሚታዘዝ ውሃ የሚጨምርና ከንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ማሽን በአንድ ወጣት ፈጠራ ተሰርቶ ለአገልግሎት በቃ።

ወጣቱ የፈጠራ ሰው ወንድማገኝ ኃይሉ  የሰራው ማሽን በእጅ መታጠብ ጊዜ ንክኪን የሚያስቀርና ሰዎች ተራርቀው እጃቸውን እንዲታጠቡ የሚያስችላቸው ነው።

ወጣቶችና ምሁራን በኮሮና  ወረርሽኝ  ጊዜ ህዝብን የሚጠቅሙ፣ በሽታውን የሚከላከሉና ሀገሪቷን የሚያሻግሩ ጭንቅላታቸውን እንዲጠበቡበት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስቀድመው ነው ጥሪ ያስተላለፉት። 

በቢሸፍቱ ከተማ  በጋራዥ ስራ  የሚተዳደረው  ወጣት ወንድማገኝ  ” ለዚህ ምላሽ ብዬ ነው የስራዬን ውጤት ይፋ ለማድረግ የበቃሁት”  ሲል ለኢዜአ ገልጿል።

በቢሸፍቱ ከተማ  በጋራዥ ስራ  የሚተዳደረው  ወጣቱ ማሽኑ ለውሃ፣ ሳሙናና ሳኒታይዘር መጨመሪያ ሶስት መክፈቻ ቧንቧዎች እንዳሉት ተናግሯል።

አጠቃቀሙም በተፈለገው የቃል ንግግር የሚታዘዝ  እንደሆነ አስረድቷል።

ማሽኖቹ ከተለያዩ የተሽከርካሪ አካላት በግብአትነት ተጠቅሞ  እንደሰራቸው ጠቅሶ አገልግሎት ሰጥቶ የሚወጣው ውሃ  ታክሞ እንደገና ለአትክልት ልማት እንዲውል ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክቷል።

ወጣቱ ፈጠራውን ከጀሪካን ጀምሮ  አሁን እስከ አንድ  ሺህ ሊትር ውሃ ወደ ሚይዝ ማሽን ማሳደጉንና ለወደፊቱም ከዚህ የተሻለ ፈጠራ ይዞ ለመቅረብ አስቧል።

የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ይረዳሉ ተብለው በጤና ባለሙያዎች  ከሚመከሩት ዋና ዋና መንገዶች አንዱ እጅን አዘውትሮ በውሃና ሳሙና መታጠብ ነው።

ለዚህም የወጣቱ የፈጠራ ስራ የበኩሉን አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ኢነርጂ ኤሪያ ተባባሪ ዲን ዶክተር ዳዊት ጉደታ ወጣቱ  የእጅ መታጠቢያ ማሽኑን  ሲሰራ  በማማከር ሲደግፉት መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር ዳዊት በሰጡት አስተያየት የወጣቱን ክህሎት በመጠቀም ለወደፊቱ የዚህን ማሽን አቅም ማሳደግ፣ ሲቀርቡት ብቻ በሴንሰር የሚሰራ የእጅ መታጠቢያና በሪሞት ኮንቶሮል የሚሰራ የበር ላይ ፍተሻ ጭምር በመሞከር ላይ  መሆናቸውን ገልጸዋል።