በሱሉልታ 10 ሺህ የሚደርሱ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ዝግጅት ተደረገ

84

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2012(ኢዜአ) በተያዘው ክረምት እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሰዎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚያከናውን በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ባለፈው ሳምንት በይፋ የተጀመረው የበጎ-ፈቃድ ወይም የዜግነት አገልግሎት በሱሉልታ ከተማም ቀጥሏል።

በክልሉ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስተባባሪነት በተካሄደው መርሃ ግብር አርቲስቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በዕለቱም የችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ተደርጓል።

የክልሉ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁሴን ዝናብ ''በተጀመረው የበጎ-ፈቃድ አገልግሎት 7 ሚሊዮን  የክልሉ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዷል'' ብለዋል፡፡   

ኃላፊው እንዳሉት፤ በተለይ የአካባቢ መራቆትን ለመግታት በዚህ ክረምት ሰፊ ሥራ ይከናወናል።

''አሁን ያለው ትውልድ ምንም እንኳን በከፊል የተሻለ አረንጓዴ ለበስ መልክዓ-ምድር ቢረከብም ለመጪው ትውልድ የተሻለ አረንጓዴ ምድርን ማውረስ ይገባል'' ብለዋል።

የሱሉልታ ከተማ ከንቲባ አቶ ሰለሞን አበበ በበኩላቸው የከተማውን ነዋሪዎች በማስተባበር 10 ሺህ ያህል በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እስከ 500 ሺህ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የደም ልገሳና የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ተግባር እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሥራዎች በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል ተነሳሽነት እንዳለውም አቶ ሰለሞን አረጋግጠዋል።

በዛሬው መርሃ-ግብር ቤታቸው የታደሰላቸው ወይዘሮ መገርቱ ደበሉ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ለ12 ዓመታት ጣራው በሚያፈስና ግድግዳው ባልተመረገ ቤት ውስጥ እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮዋ፤ "የቤት እድሳቱ ለእኔ ከሞት የመነሳት ያህል ነው" ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የቤት ዕድሳቱን ከማከናወን ባለፈ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሰጥቷቸዋል።

አቶ ያሬድ አወቀ የተባሉ ባለሃብት በበኩላቸው ለወይዘሮ መገርቱ የአንድ አመት ቀለብ ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።

እንደ አቶ ያሬድ ገለጻ፤ ድርጅታቸው በሱሉልታ ከተማ ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ላለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ችግኝ እየተከለና እየተንከባከበ እንደሆነም ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የኦሮሞ አርቲስቶች ሕብረትን ወክሎ የተገኘው አንጋፋው ድምጻዊ ጸጋዬ ደንደና ''የጥበብ ሰዎች በሙያቸው በጎ ፈቃደኝነትን ሊያግዙ ይገባል'' ብሏል።

በተለይ ደግሞ የታለመውን የአረንጓዴ አሻራ እውን ለማድረግ አርቲስቶች ሙያቸውን ተጠቅመው 'የሕዝብ ንቅናቄ'  ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝቧል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የሚከናወነውን የበጎ-ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብርን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወሊሶ ከተማ ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም