ባለሥልጣኑ በአገር አቀፍ ደረጃ 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችለውን መርሃ

84

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በአገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችለውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር አስጀምሯል፡፡

ባለሥልጣኑ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩን ያስጀመረው በጉለሌ የእጽዋት ማዕከል በተዘጋጀለት ሥፍራ ነው፡፡

በማዕከሉ የተተከሉት ችግኞች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው አገር በቀል የዛፍ ችግኞች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ተገኝ ''በባለሥልጣኑ የተተከሉ ችግኞች እንክብካቤና ቁጥጥር ተደርጎላቸው እንዲጸድቁ ሠራተኞችን በማነሳሳት ክትትል ይደርጋል'' ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ በዚህ ዓመት ሁለት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እንዳቀደ የገለጹት ኢንጂነር ሐብታሙ፤ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ግንባታ ዛፍ መቁረጥ እንዳለ ተናግረዋል።

ይህንን የሚቆረጥ ዛፍ ለመተካት ደግሞ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ተንከባክቦ የማጽደቅ ባህል እንዲዳብር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በባለሥልጣኑ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉት ፕሮጀክቶች የሚተከሉ ችግኞችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲይዛቸው እየተደረገ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የአካባቢ፣ ማህበራዊ እና የሥራ ቦታ ደህንነት ዳይሬክተር ኢንጂነር ገነት ዓለማየሁ በበኩላቸው ''ለአገራዊው 5 ቢሊዮን የመትከል አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለስልጣኑ የድርሻውን ይወጣል'' ብለዋል።

ለዚህም ባለሥልጣኑ በአገሪቱ ባሉት ቅርንጫፎችና ፕሮጀክቶች ሁለት ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ በዛሬው ዕለት የማብሰሪያ ተከላ መካሄዱን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን የሚከውነው የኮሮናቫይረስ ተጋላጭነት እንዳይኖር ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንደሆነም አመልክተዋል።

ታላላቅ አገራዊ የግድብ ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡና የአየር ንብረት ሚዛንንም ለመጠበቅ እንዲቻል ሁሉም ህብረተሰብ የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎውን እንዲያሳርፍም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፎ ያደረጉ የባለስልጣኑ ሰራተኞች ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብም እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።

በእለቱም የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች 500 ችግኞችን የተከሉ ሲሆን፣ በመላ አገሪቱ ባሉት ቅርንጫፍና ፕሮጀክቶች ከ200 እስከ 500 ሺህ የሚሆኑ ችግኞችን እንደሚተክሉም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም