የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶች በአቅራቢያቸው ማግኘት እንዳልቻሉ አርሶ አደሮች ተናገሩ

40

አክሱም፣  ሰኔ 15/2012ዓ.ም /ኢዜአ/ በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ መከላከያ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አቅርቦት አርሶ አደሩን ጭምር ያካተተ እንዲሆን ጥያቄ ቀረበ ።

በላዕላይ ማይጨው ወረዳ የደብረ ብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በሪሁ ተወልደ በሰጡት አስተያየት የኮሮና  ቫይረስ ለመከላከል እጃቸውን በሳሙና በመታጠብና ከንክኪ በመራቅ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ሌሎች አማራጮች ግን እያገኘን አይደለም ብለዋል ።

የከተማ ሰዎች የሚጠቀሙበት የንፅህና መጠበቂያ አልኮልና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዳንጠቀም ግን የእውቀቱም ሆነ በአካባቢያቸው የአቅርቦት ችግር መኖሩን ተናግረዋል ።

ቁሳቁሶች ለመግዛት ብናስብም ወደ ከተማ ብንሔድ በኮሮና ቫይረስ እንጠቃለን በሚል ስጋት ደፍረን ገበያ መውጣት አልቻልንም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

በመሆኑም ለአርሶ አደሩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በየገበሬ ማህበሩ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል ።

በዓድዋ ወረዳ የታሕታይ ለጎምቲ አርሶ አደር ሳህለ መኮነን በበኩላቸው በቤተ እምነቶች  ህዝቡ በብዛት እንደሚሰበሰብ ገልጸው የፊት መሸፈኛ ጭምብል ለመጠቀም ቢፈልጉም አቅርቦቱ የለም ብለዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከመከላከል ጎን ለጎን የግብርና ስራቸውን በማቀላጠፍ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በታሕታይ ማይጨው ወረዳ የሸዊት ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሴት አርሶ አደር ምጽላል ትኩእ ናቸው።

የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ይረዳሉ የተባሉ ፈሳሽ የንፅህና መጠበቂያዎችና  የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በአጠቃቀሙ ግንዛቤ እንደሌላቸው ገልፀው አቅርቦቱም ጭምር አለመኖሩ አስረድተዋል ።

መንግስት አጠቃቀሙና አቅርቦቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በትግራይ ማዕከላዊ ዞን የኮሮና መከላከል ግብረሃይል የኢኮኖሚ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ጽገ ተስፋይ እንደገለፁት በዞኑ ከሳምንታት በፊት የነበረው የአልኮልና የጭንብል እጥረት መፈታቱን ገልጸዋል።

በገጠር የኮሮና መከላከያ ቁሳቁሶች አቅርቦት ችግር እንዳለ ተገምግሞ በዚህ ሳምንት በዞኑ ባሉት ከ900 በላይ የህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት የአቅርቦት ስራው እንዲጀምር ይደረጋል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የመከላከያ ቁሳቁስ በአቅራቢያው የሚያገኝበት እድል እየተመቻቸ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም