በአርባምንጭ ከተማ በበጀት ዓመቱ 1ሺህ 910 ሰዎች የሥራ ዕድል አገኙ

1777

አርባምንጭ፣ ሰኔ 13/2012 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ በበጀት ዓመት በኢንተርፕራይዝ የተደራጁ 1ሺህ 910 ሰዎች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን የከተማው አስተዳደር ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የስራ እድሉን ያገኙት በ224 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ሰዎች ነው።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታፌታ ደሰለ ለኢዜአ እንደተናገሩት ለሰዎቹ በተመቻቸላቸው መደበኛና ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡

የተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች ግንባታ፣ ማኑፋክቸርንግ፣ አገልግሎት፣ ንግድ እና ከተማ ግብርና ናቸው።

ወደ ስራ ለገቡትም በመንግስት ብቻ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ዕድል የተመቻቸላቸው መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በማኑፋክቸርንግ ዘርፍ፣ በዳቦ እና እንጀራ ጋጋሪነት የተሰማሩ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ምርታቸውን ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እንዲያቀርቡ እንዲሁም የአፍንጫና አፍ መሸፈኛ ጭምብል በማምረት ለገበያ እንዲያቀርቡ ዕድል የተመቻቸላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በግንባታ ዘርፍ የተሰማሩ ደግሞ ለከተማ ልማት ፕሮግራም ከዓለም ባንክ በሚለቀቅ ገንዘብ በድንጋይ ንጣፍ መንገድ፣ አረንጓዴ ልማትና በውሀ ማፋሰሻ ግንባታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገበያ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ግንባታ በመደበኛው ካፒታል ተጫርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑም ተመቻችቶላቸዋል።

በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ ከገቡ ማህበራት መካከል የ“ፀሐይ ብርሃን ኮንስትራክሽን” ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ፀጋው ኃይሌ  በሰጠው አስተያየት ሦስት ማህበራት በጋራ የሁለት ሚሊዮን 500ሺህ ብር ሥራ እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

መንግስት በቀጥታ የሥራ ዕድል ከመፍጠርም በላይ በጨረታዎች እንዲሳተፉ ፍትሃዊ አሠራር መዘርጋቱንም ጠቁሟል።

በተጨማሪም በሂሳብ መዝገብ አያያዝ እንዲሁም የማህበሩን አጠቃላይ የግንባታ ሥራ በሚመለከት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ጠቅሷል።

ከሌሎች ጋር በመሆን በግላቸው ባዋጡት አንድ መቶ ሺህ ብር ወደ ስራ በመግባት  በዓመት ካፒታላቸውን  አንድ  ሚሊዮን ብር ማድረሳቸውን የገለጸው ደግሞ “እሙሽ እንጨትና ብረታ ብረት ስራ ማህበር” ኃላፊ ወጣት ለአምላክ ይሁን ነው፡፡

ጠንክረው በመስራት ውጤታማ መሆን እንደቻሉ ያመለከተው ወጣቱ ለመስሪያና መሸጫ ቦታ ኪራይ የሚያወጡት ብዙ በመሆኑ መንግስት እንዲደግፋቸው መፈለጋቸውን ተናግሯል።

ወደ ስራ የገቡት ኢንተርፕራይዞቹ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል መንግስት እያከናወነ ያለውን ስራ ለማገዝ ከ126 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡