የአዋጁ ክልከላዎች ማክበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍቶችን ለማስተካካል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

59

ጎባ፣ ሰኔ 14/2012( ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላዎች ማክበር ላይ የሚስተዋሉ ክፍቶችን ለማስተካከል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የባሌ ዞን ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጸ።

ክልከላዎችን ተላልፈው በተገኙ 115 ግለሰቦች በገንዘብና እስራት እንዲቀጡ መደረጉም ተመልክቷል፡፡

የግብረ ኃይሉ አባልና የዞኑ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልዋሂድ አብዱረህማን ለኢዜአ እንደተናገሩት የቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከጤናና ፍትህ አካላት ጋር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ  ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ህብረተሰቡ በስፋት በሚሰበሰብባቸው ገበያ፣ ባንክና የከተሞች ዋና ዋና መንገዶች ላይ በበሽታው መተላላፍያ፣ አስከፊነትና መደረግ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች ላይ ሰፊ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

መንግስት ማህበረሰቡን ከቫይረሱ ለመታደግ ያወጣውን አዋጅ  ክልከላዎች እንዲከበሩ በየደረጃው በሚገኙ የፍትህ አካላት ትምህርት እየተሰጠ ነው።

ክልከላዎችና ደንቦች የሚጥሱ አካላት ላይ ለህዝብና ሃገር ደህንነት ሲባል አስተማሪ እርምጃዎች መውሰድና ህግ የማስከበር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

እስካሁንም በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች 115 ግለሰቦች  ክስ ተመስርቶባቸው እንደ የጥፋታቸው ከአንድ ሺህ ብር እስከ አምስት ወር በሚደርስ እስራት ቅጣት መደረጉን አቶ አብዱልዋሂድ ጠቅሰዋል።

ይህም ቅጣት ርቀትን ባለመጠበቅና የአፍ አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያልተጠቀሙ ግለሰቦች እንዲሁም በእምነት ተቋማትና መሰል አካባቢዎች ተሰባስበው በተገኙ ሰዎች ላይ የተወሰደ እርምጃ ነው።

የቫይረሱ ስርጭት እየከፋ በመምጣቱ የወጡ ክልከላዎች በመተግበር ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንደለበትም አመልክተዋል።

በአፈጻጸም ሂደት የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ መለሰ አብረሃም በሰጡት አስተያየት የአዋጁ ደንቦችና መመሪያዎች ዓላማ የህብረተሰቡን ደህንነትና ጤንነት በመጠበቅ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለማስቀረት መሆኑን ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው በአሁኑ ወቅት ሰዎች የአዋጁን ክልከላዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ እያደረጉ እንዳልሆነ  መታዘባቸውንና ይህ ጉዳይ እልባት ካልተሰጠው ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ የራሱን ደህንነት ለማስጠበቅ ህጉን ማክበር እንዳለበት ያሳሰቡትዳኛው ክልከላዎችን በሚተላለፉ ግለሰቦች ላይ አስተማሪ ቅጣት በመጣል አደጋውን ለመቀነስ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በአካባቢያቸው ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ክልከላዎች በማክበር ረገድ ክፍተቶች እንደሉ የገለጹት ደግሞ በዞኑ የሲናና ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ጄይላን ከዲር ናቸው፡፡

ገበያ፣ለቅሶ ቤት፣ ሆቴል፣ ባንኮችና የትራንስፖርት አገልገሎት መስጪያ ስፍራዎች ሰዎች በጋራ በመሰባሰብ ክልከላዎቹ በስፋት ከሚጣስባቸው አካባቢዎች መካከል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሲናና ወረዳ አቃቤ ህግ አቶ እሸቱ ግዛው በበኩላቸው በመጀመሪያ አከባቢ እጅን በተደጋጋሚ ለመታጠብና ርቀትን  ለመጠበቅ ጥረት ሲደረግ የነበረው ሁኔታ እየተዘነጋ መምጣቱን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ከቸልተኝነት በመውጣት ሁሉም ለራስ ሲል ጥንቃቄ ማድረግና መመሪያዎችን ማክበር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

መንግስት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዜጎቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም