የምስራቅ ሸዋ ዞን ዘመናዊ የመኖ ልማትና እንስሳት እርባታ ማስፋፋት ይገባል

232

አዳማ ፣ ሰኔ 14/2012 ( ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ ዘመናዊ የመኖ ልማት እና እንስሳት እርባታ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ማስፋፋት እንደሚገባ ተመለከተ።

የጨፌ ኦሮሚያ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በምስራቅ ሸዋ ዞን በዘርፉ እየተከናወነ ያለውን ልማት ዛሬ በመስክ ተመልክቷል።

በምስክ ጉብኝቱ ወቅት የኦሮሚያ እንስሳት ሀብት ልማት ኤጄንሲ ኃላፊ ዶክተር ተስፋዬ በቀለ  “የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማዘመን መነሻችን የመኖ አቅርቦት መሆን አለበት “ብለዋል።

ዶክተር ተስፋዬ እንዳሉት በተለይ በምስራቅ ሸዋ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ከዘመናዊ የእንስሳት ከእርባታ እርባታ በተጓዳኝ በመኖ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ መደረጉ ለዘርፉ ልማትና እድገት ቀጣይነት ተስፋ የሚሰጥ ነው።

ይህ የተቀናጀና በቴክኖሎጂ  የታገዘ ዘመናዊ የመኖ ልማትና  እንስሳት እርባታ በክልሉ ቆላማ ዞኖች ምሳሌ የሚሆንና ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምስራቅ ሐራርጌን ጨምሮ ለሌሎች የክልሉ ዞኖች ያለባቸውን የእንስሳት መኖ ችግር ለማቃለል  ከዞኑ ልምድ በመቅሰም ወደ ራሳቸው ወስደው ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን የእንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሐመድ ሀሰን በበኩላቸው ዞኑ የእንስሳት መኖ እጥረት በስፋት የሚታይበት ከመሆኑም ባለፈ ቆላማና  በድርቅ የሚጠቃ ነው ብለዋል።

በዚህም በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የእንስሳት ሀብት በመኖ እጥረት ምክንያት ለጉዳት ይጋለጣሉ።


ችግሩን ለማቃለል 8ሺህ 200 ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

እነዚህ አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም  በማደራጀት  በመኖ ልማት ላይ ጭምር ተሰማርተዋል።

ልማቱ እየተካሄደ ያለው የእንስሳት ሀብት በስፋት በሚገኝባቸው  ቦራ፣ ዱግዳ፣ ሉሜ፣ ቦሰት፣ ፈንታሌና አዳሚ ቱሉ ወረዳዎች ውስጥ እንደሆነ ተመልክቷል።

በዞኑ ቦራ ወረዳ ጎራ ለማን ቀበሌ  አርሶ አደር ነምጉዱ እሬሳ  በሰጡት አስተያየተ በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ እያለሙ  መሆኑን ተናግረዋል።

አምና 32 ከብቶች በድርቅ ምክንያት  እንዳሉቁባቸው ጠቅሰው ችግሩን ለመቋቋም ወደ መኖ ልማት መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

በዓመት ከአምስት ጊዜ በላይ የሚደርስ የእንስሳት መኖ በማልማታቸው ከ200 በላይ የጋማ ከብቶች፣በጎችና ፍየሎች እየመገቡ ማርባታቸውን ቀጥለዋል።

ከዚህ ባለፈም  በዓለም ጤና ከተማ በእንስሳት እርባታ ለተሳተፉ ባለሀብቶች አንድ እስር  መኖ እስከ 120 ብር እየሸጡ መጠቀማቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የመኖውን ዘር በኪሎግራም በ200 ብር ቦራ ወረዳና የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ጨምሮ ሌሎች በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶችና አርሶ አደሮች እየሸጡ መሆኑን አመልክተዋል።


የቋሚ ኮሚቴው  ሰብሳቢ አቶ አበራ አየለ በተለይ  ቆላማ የሆኑ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምስራቅ ሐራርጌ፣ ከፊል ባሌ ዞንና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሰፊ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በየጊዜው በሚከሰተው ድርቅ  የመኖ እጥረት እያጋጠመ ጉዳት እንደሚደርስ ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን  ዘመናዊ የእንስሳት እርባታና መኖ ልማት በተቀናጀ መንገድ ችግርን ለመፍታት ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች በማስፋፋት የዘርፉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ወሳኝ ሚና ያለው ነው ብለዋል።

ቋሚ ኮሚቴ በምስራቅ ሸዋ ዞን  በዘርፉ እየተከናወነ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ የተመለከተው  በቦራ፣ሉሜና አዳማ ወረዳዎች ውስጥ ነው።