በምስራቅ ጎጃም አሲዳማ አፈርን ለማከም የኖራ አቅርቦት እጥረት አጋጠመ

ደብረማርቆስ፣ ሰኔ14/2012 (ኢዜአ ) አሲዳማ አፈርን በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዛቸው የኖራ አጥረት በማጋጠሙ መቸገራቸውን በምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

 የዞኑ ግብርና መምሪያ በበኩሉ እጥረቱን ለማቃለል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።

አርሶ አደር ገናነው አዲስ በአነደድ ወረዳ የንፋሳም ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ከአንድ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬታቸው አሲዳማ አፈር በመሆኑ በኖራ ካልታከመ ምርት መስጠት እንደማይችል በተሞክሮ ማረጋገጣቸውን ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

መሬታቸውን የግብር ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ምክር መሰረት አክሞ ምርታማ ለማድረግም ከ20ኩንታል በላይ የአሲዳማ አፈር ማከሚያ ኖራ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክተዋል።

ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የተሰጣቸውን 11 ኩንታል ኖራ ከመሬታቸው ላይ በመበተን ቢቀላቅሉም የግብርና ባለሙያዎች ከሚሰጡት ምክረ ሃሳብ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ  በመሆኑ በምርታማነት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድርባቸው ሰግተዋል።

በጎዛምን ወረዳ የእነራታ ቀበሌ አርሶ አደር ታዘበው ገድፍ  በበኩላቸው ኖራ አሲዳማ አፈርን በማከም ለምርት እድገት አስፈላጊ ቢሆንም መንግስት በበቂ ሁኔታ እንዳላቀረበላቸው ገልጸዋል።

ከሶስት ሄክታር በላይ ማሳቸው በአሲድ የተጠቃ በመሆኑ እስከ 40 ኩንታል ኖራ ቢያስፈልጋቸውም እስካሁን የቀረበላቸው 25 ኩንታል ነው ብለዋል።

ይህም የሚጠብቁትን ምርት ማግኘት እንደማያስችላቸው ተናግረዋል።

መንግስት በየዓመቱ ማነቆ የሆነባቸውን የግብአቱ ችግር ትኩረት በመስጠት እንዲፈታላቸው አርሶ አደሮቹ አመልክተዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አበባው እንየው በምርት ዘመኑ ከአንድ ሺህ 500ሄክታር በላይ ለአሲዳማነት የተጋለጠን ማሳ በማከም የሚጠበቀው የምርት እድገት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መሬቱን በሳይንሳዊ መንገድ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ከ30ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረት ከሚያስፈልገው ውስጥ ከስምንት ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ማቅረባቸውን ጠቁመው የጋጠመውን እጥረት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ለሰብል ልማት ከሚውለው ከ650ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከ160ሺህ በላይ የሚሆነው አሲዳማ መሆኑን ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም